ሀገርን በእውቀት ለመገንባት የሴት ምሁራን ሚና…
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገር ግንባታ ሂደት እየተመዘገቡ ላሉ ድሎች ሴት ምሁራን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው አሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፡፡
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) “የሴቶች ድምጽ ለእኩልነትና ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተከብሯል።
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በእውቀት ላይ ለተመሰረተ የሀገር ግንባታ ሂደት የሴት ምሁራን ሚና የላቀ ነው፡፡
ቀደም ባለው ጊዜ እናቶች ምንም ሳይማሩ ለሴቶች እኩልነት የላቀ ሚና መወጣታቸውን አስታውሰው፥ አሁን ላይ ሴቶች የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ሴት ምሁራን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የጅማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጠሃ ቀመር በበኩላቸው፥ ሴቶች የሀገር ኢኮኖሚ መሰረት በመሆናቸው ለሀገረ መንግስት ግንባታ የሴቶችን እኩል ተሳትፎ ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
ሴቶች መምህራን የምርምርና የፈጠራ ዘርፍ ፕሮጀክቶችን እንዲመሩና አዳዲስ ፈጠራዎችን እንዲያበረክቱ እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀማል አባፊጣ (ዶ/ር) ናቸው።
ዩኒቨርሲቲው ለማህበረሰብ ጥቅም የሚያመጡ ድጋፍና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በበዓሉ በኢትዮጵያ የ50 ዓመታት የለውጥ ጉዞና የሴቶች ቀን ታሪካዊ ፋይዳ የተመለከተ ጥናታዊ ጹሁፍ ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን፥ ሴቶችን ብቻ ያሳተፈ የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሄዷል።
በወርቅአፈራው ያለው