Fana: At a Speed of Life!

መገናኛ ብዙሃን ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር በትብብር መስራት አለባቸው – ወ/ሮ ኃይማኖት ዘለቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መገናኛ ብዙሃን ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር በትብብር መስራት አለባቸው አሉ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ኃይማኖት ዘለቀ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማሕበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሙዓዘ ጥበባት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፣ የመገናኛ ብዙሃን አመራሮች እና ሌሎች ባለድርሻዎች በተገኙበት መገናኛ ብዙሃን በሀገር ብሔራዊ ጥቅም ላይ ያላቸውን ሚና የሚዳስስ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

ወ/ሮ ኃይማኖት ዘለቀ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ተመዝግበው እና ዕውቅና አግኝተው የሚንቀሳቀሱ መገናኛ ብዙሃን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃኑ ለብሔራዊ ጥቅም መከበር የጎላ ሚና እንዳላቸው ገልጸው፤ ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና ሚዛናዊ ዘገባ በማቅረብ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የሀገር ብሔራዊ ጥቅም እንቅፋት የሆኑትን የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት መከላከል ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም መገናኛ ብዙሃኑ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን በመከላከል ትክክለኛውን ዳራ ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበው፤ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር በትብብር መስራት አለባቸው ነው ያሉት።

የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል በትኩረት እንደሚሰራ ነው የተናገሩት።

በዲጂታል ሚዲያ አማራጮች የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃዎችን በቴክኖሎጂ አማካኝነት ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም መገንባቱን ጠቅሰዋል።

ባለስልጣኑ መገናኛ ብዙኃንን መደገፍ፣ ማብቃትና ማረም ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸው፤ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳ ተግባር በሚፈጽሙት ላይ ህጋዊ ርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

በተለይም የዲጂታል ሚዲያ አውታሮችን ተጠቅመው ሀሰተኛ፣ መሰረተ ቢሰና የጥላቻ መረጃን የሚያሰራጩ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ላይ አስተማሪ ርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.