በአማራ ክልል በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከ65 ሺህ በላይ ተገልጋዮች ተስተናገዱ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከ65 ሺህ በላይ ተገልጋዮች ተስተናግደዋል አለ የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ።
በቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ታደለ ልደት ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ በቀደመው የወረቀት አገልግሎት አሳጣጥ በተቋማት አገልግሎት ለማግኘት የሚመጡ ባለጉዳዮች ከፍተኛ እንግልት ሲገጥማቸው ነበር።
ተገልጋዮች የሚያነሷቸውን ቅሬታዎች ለመፍታት በተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተለያዩ የክልሉ ተቋማት አገልግሎታቸውን በአንድ ቦታ እየሰጡ ነው ብለዋል።
ከክልሉ ማዕከል ባለፈ በባሕር ዳርና ደሴ ከተሞች በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው÷ በዚህም ባለፉት 6 ወራት ከ65 ሺህ በላይ ባለጉዳዮች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዲጂታል ስርዓት የሚሰጠው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከተጀመረ ወዲህ የደንበኞች የእርካታ ወደ 97 በመቶ ከፍ ማለቱንና ተገልጋዮች በየተቋማቱ የሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች ትርጉም ባለው መልክ እየተፈቱ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።
በክልሉ በ2ኛው ዙር 5 ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አንስተው÷ የጎንደር ከተማ ማዕከል ግንባታ እየተጠናቀቀ እንደሚገኝና በቅርቡ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ገልጸዋል።
በተጨማሪም በ3ኛው ዙር 25 ከተሞችን ስራ ለማስጀመር ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አመልክተዋል።
በምናለ አየነው