የኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ ለአካባቢው ማህበረሰብ ሰፊ የስራ እድል ይፈጥራል – መሐመድ አብዱራህማን (ኢ/ር)
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ ለአካባቢው ማህበረሰብ ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥር ፕሮጀክት ነው አሉ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ መሐመድ አብዱራህማን (ኢ/ር)፡፡
የ’ገበታ ለትውልድ’ ውጥን አካል የሆነውን ‘ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት ተመርቋል፡፡
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መሐመድ አብዱራህማን (ኢ/ር) እንዳሉት÷ የአፋር ክልል የድንቅ ባህላዊ እሴቶች፣ የተፈጥሯዊ መስህቦች፣ የቀደምት ስልጣኔዎች መዳረሻ እና የቀደምት ፍጥረታት መገኛ ነው፡፡
በክልሉ ያሉ ድንቅ የተፈጥሮ ስፍራዎችን በዘመናዊ መልኩ ለማሳየት መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው÷ በገበታ ለትውልድ የተቀናጀ የቱሪስት መዳረሻ የሆነው የኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ የትኩረቱ አንድ አካል ነው ብለዋል፡፡
138 ኪሎ ሜትር ላይ ያረፈው ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ በስተምስራቅ አቅጣጫ 222 ኪሎ ሜትር በአፋር ክልል ውስጥ እንደሚገኝ እና የፍል ውሃ ምንጮችና የዘንባባ ዛፎች የሎጁ ልዩ መገለጫዎች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
የሎጁ ግንባታ የክልሉን ትምህርታዊ፣ ትውፊታዊ፣ ባህላዊ እንዲሁም የቱሪዝም እና የኢኮኖሚ እሴቶችን ጠብቆ በማደስ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ ሁለት የሄሊኮፕትር ማረፊያ፣ 6 ሄክታር የሚሸፍን ሰው ሰራሽ ሀይቅ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ህንፃዎች፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የደን ልማት ስራዎች እንዲሁም የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ ሰፊ የስራ እድል እንደሚፈጥር ገልጸው÷ ይህም ለክልሉ ዘላቂ ልማትና ብልፅግና ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተገነቡ ያሉ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የቱሪዝም ዘርፉን እምቅ አቅም የገለጡ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ ፕሮጀክቶቹ ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻነቷን ይበልጥ እንድታሳድግ የሚያግዙ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ