Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጦርነቱን የማስቆም መነሻ ሀሳብ ሲያቀርቡ፤ ኢራን ምንም ድርድር የለም ብላለች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱን ለማስቆም በሚል 15 ነጥብ ያለው የመነሻ ሀሳብ ይፋ ቢያደርጉም፤ ኢራን ምንም ዓይነት የድርድር ሂደት እንደሌለ አስታውቃለች።

የትራምፕ አስተዳደር ጦርነቱ እያስከተለ በሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ችግር ምክንያት አሜሪካ ከኢራን ጋር የሚደረገውን ጦርነት በፍጥነት ለማስቆም ያስችላል ያለውን ባለ 15 ነጥብ መነሻ ሃሳብ ይፋ አድርጓል።

ከኢራን ጋር ለመነጋገር ጥረት እየተደረገ መሆኑ እና ጦርነቱን ለማስቆም የቀረበው መነሻ ሀሳብ በፓኪስታን በኩል ወደ ኢራን መላኩ ተዘግቧል።

ፓኪስታን የአደራዳሪ ሚናን በመያዝ እየሰራች እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህም ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣናት በውይይቱ እየተሳተፉ እንደሆነ ተመላክቷል።

በአሜሪካ ከቀረበው ባለ 15 ነጥብ የጦርነት ማስቆም መነሻ ሀሳብ መካከል፦

◉ በኢራን ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች ማንሳት፣

◉ አሜሪካ በኢራን ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሚሆን የሲቪል የኑክሌር ፕሮግራም መደገፍ፣

◉ ወደፊት የሚጣሉ ማዕቀቦች ስጋት አለመኖር፣

◉ ኢራን ያሏትን ኑክሌር የማበልጸግ ስራ እንዲቆም በሀገሪቱ ውስጥ ምንም ዓይነት የዩራኒየም ማበልጸጊያ መሠረተ ልማት እንዳይኖር ማድረግ፣

◉ የናታንዝ፣ የኢስፋሃን እና የፎርድ የኑክሌር ተቋማት እንዲፈርሱ ማድረግ፣

◉ ኢራን የዩራኒየም ክምችቷን ለዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (አይኤኢኤ) እንድታስረክብ ማድረግ፣

◉ አይኤኢኤ ጥብቅ እና ቋሚ የቁጥጥር ስርዓትን እንድትቀበል እና ተቆጣጣሪዎች ወደ ኑክሌር መሠረተ ልማቶች በነፃነት እንዲገቡ መፍቀድ፣

◉ ኢራን ለታጣቂ ቡድኖች የምታደርገውን የገንዘብ እና ወታደራዊ ድጋፍ ማቆም፣

◉ የኢራን የሚሳኤል ፕሮግራም ልማት በከፍተኛ ደረጃ እንዲገደብ እና የሚሳኤል አጠቃቀሟን ለራስ መከላከያ ብቻ እንዲሆን መገደብ፣

◉ እንዲሁም የሆርሙዝ ሰርጥ ክፍት ሆኖ እንዲቆይ ማድረግን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮችን ያካተተ መሆኑን ኒውዮርክ ፖስት በዘገባው ገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢራን ጉዳዩን አስመልክቶ ከአሜሪካ ጋር እየተደረገ ያለ ምንም ዓይነት ግንኙነት አለመኖሩን ገልጻለች።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ኢራን ጦርነቱን ለማስቆም ስምምነት ላይ ለመድረስ ዝግጁ እንደሆነች መግለጻቸውን ተከትሎ የኢራን መንግስት “አሜሪካ እየተደራደረች ያለችው ከራሷ ጋር ነው” ማለቱን አልጀዚራ ዘግቧል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.