Fana: At a Speed of Life!

አርዓያ የሚሆን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጉዞ…

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባትና የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ በምታደርገው ጥረት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽግግርን በማጠናከር ላይ ትገኛለች።

በአፍሪካ ከሚገኙ ተሽከርካሪዎች ብዙሃኑ ያረጁና በነዳጅ የሚሰሩ በመሆናቸው የነዳጅ ወጪን ጨምሮ በአህጉሪቱ ኢኮኖሚና የአየር ንብረት ተጽዕኖን የመቋቋም ጥረት ላይ ጫና እያሳደረ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን ጫና በመገንዘብ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ፖሊሲ ጭምር ቀርጻ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በብዛት ለመጠቀም ማበረታቻዎችን እያደረገች ትገኛለች፡፡

በቢዝነስና የፈጠራ ልማት ላይ ትኩረቱን ያደረገው ߵኔክስት ቢሊየንߴ ድረገጽ ባወጣው ሀተታ፥ ኢትዮጵያ ለሌሎችም ሀገራት አብነት የሚሆን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጉዞ ላይ መሆኗን አስነብቧል፡፡

በፈረንጆቹ 2030 በኢትዮጵያ የሚገኙ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር 400 ሺህ ለማድረስ እየተሰራ ያለው ስራ ወሳኝ ሂደት ላይ መሆኑን አመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል የምታመነጨው ከውሃ ሀብቷ በመሆኑ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጉዞዋ በጠንካራ የታዳሽ ኃይል አቅም የተደገፈ መሆኑንም አስረድቷል፡፡

ይህም አስተማማኝና ወጪ ቆጣቢ ኃይል በማቅረብ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽግግር መሰረት የሚጥል እንደሆነም ተመላክቷል፡፡

በዚህ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ሽግግር ሂደት በተለይም ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል አቅርቦት መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ረገድ የተጀመሩ ስራዎችን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚጠበቅባት ጠቁሟል፡፡

ከኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኃይል መሙያ ጣቢያዎች በተጨማሪ እንደ ዶዳይ ያሉ ኩባንያዎች ቻርጅ የተደረጉ ተለዋጭ ባትሪዎችን በማቅረብ አማራጭ ይዘው መጥተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪዎችን የሚያቀርበው ዶዳይ ኩባንያ መስራች የሆኑት ዩማ ሳሳኪ እንደሚሉት፥ ኩባንያቸው በኤሌክትሪክ ለሚሰሩ ሞተር ሳይክሎች የባትሪ መለዋወጥ ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል፡፡

ይህ ቴክኖሎጂ ባትሪዎችን ቻርጅ ለማድረግ የሚወስደውን ጊዜ ከመቆጠብ በተጨማሪ የባትሪ ቻርጅ ማድረጊያ መሰረተ ልማት ውስንነትን ለመቅረፍ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኩባንያው በዚህ ዓመት በአዲስ አበባ 100 የኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክል ባትሪ መለዋወጫ ጣቢያዎችን ለመክፈት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፥ በቀጣይም በሦስት ዓመታት ውስጥ ጣቢያዎቹን 300 የማድረስ እቅድ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ንፁህ፣ ቀልጣፋና ዘላቂ የትራንስፖርት ሥርዓት የምታደርገውን ሽግግር ለማረጋገጥ መሰል ፈጠራዎችን ማጠናከር በፖሊሲ መደገፍ ወሳኝ መሆኑንም ߵኔክስት ቢሊየንߴ በዘገባው አመልክቷል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.