በዜጎች ላይ የ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ጉዳት ባደረሱት የፊንቴክ ኢንቨስትመንት ድርጅት መስራችና ባለቤቶች ላይ ክስ ተመሰረተ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዜጎች ላይ የ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ጉዳት ባደረሱት የፊንቴክ ኢንቨስትመንት ድርጅት መስራችና ባለቤቶች ላይ ምርመራ አጣርቶ ለዐቃቤ ሕግ በመላክ ክስ ተመስርቷል አለ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ።
ፊንቴክ ኢንቨስትመንት የግል ድርጅት መስራችና ባለቤቶች ዳንኤል ዮሃንስ ኢየሱስ እና ግርማይ ገ/ሚካኤል ይህደጎ የተባሉት ተጠርጣሪዎች ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን በመጠቀም ከ1 ሺህ 200 በላይ ዜጎችን በማጭበርበር የ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ጉዳት በማድረሳቸው በ19 ዓይነት የተለያዩ ወንጀሎች ምርመራ አጣርቶባቸው ለዐቃቤ ሕግ በመላክ ክስ መመስረቱን ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።
መጀመሪያ ክሱ የቀረበው ለአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ቢሆንም ምርመራው ውስብስብና ከፍተኛ ልምድ የሚጠይቅ ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ በተደራጀ መልኩ መጣራት ስላለበት ጉዳዩን ወደ ኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በማምጣት ምርመራው በስፋት ሲጣራ መቆየቱን ፖሊስ ገልጿል።
ተጠርጣሪ ዳንኤል ዮሃንስ ላይ ክስ ተመስርቶበት ማረሚያ ቤት ሆኖ ክሱን እንዲከታተል መደረጉንና ተጠርጣሪ ግርማይ ገ/ሚካኤልን ደግሞ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
ፌደራል ፖሊስ ግርማይ ገ/ሚካኤል የተባለው ግለሰብ ከዚህ ቀደም እ.ኤ.አ በ2010 የደቡብ አፍሪካ የዓለም የእግር ኳስ ሻምፒዮና ወቅት አስካሉካን በተባለ ድርጅት ስም ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄዳችሁ የዓለም ዋንጫ እንድትመለከቱ አደርጋለሁ በማለት ዜጎችን አጭበርብሮ በሚሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ ካሰባሰበ በኋላ ተደብቆ ከሀገር በመውጣቱ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖል ጋር በመተባበር ባደረገው ጠንካራ ክትትል ከተደበቀበት ሀገር ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ አድርጎ በሕግ አግባብ ተጠያቂ እንዲሆን ማድረጉን የወንጀል ሪከርዱ እንደሚያመላክት አስረድቷል።
ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ተጎጂዎችን 50 ፐርሰንት ቅድመ ክፍያ 950 ሺህ ብር በማስከፈል በ90 ቀናት ውስጥ የመኪና ባለቤት እንደሚያደርጓቸውና ቀሪ 950 ሺህ ብር ደግሞ ያለወለድ በ5 ዓመት ተከፍሎ የሚያልቅ የባንክ ብድር እንደሚያመቻቹላቸው በመግለጽ ዜጎችን በማጭበርበር ክፍያውን እንዲፈጽሙ አድርገዋል ሲል የፌደራል ፖሊስ ገልጿል።
ተጠርጣሪዎቹ ሕብረተሰቡን ለማሳመን 148 መኪኖች ከጅቡቲ በማስገባት 100 መኪኖች ለተወሰኑ ግለሰቦች እንዲከፋፈል በማድረግ እና ቀሪ 48 ዘመናዊ መኪኖችን መርጠው በድብቅ መሸጣቸውን እንዲሁም ወደ ሀገር ውስጥ ስለመግባታቸው ምንም አይነት መረጃና ማስረጃ ሳይኖር 350 መኪኖችን ከውጭ እንዳስገቡ በማስመሰል ሲያጭበረብሩ እንደነበር ፖሊስ በምርመራው አረጋግጧል፡፡
በተጨማሪም በጅቡቲ ወደብ ምንም ዓይነት መኪና ሳይኖር 400 መኪኖች ጅቡቲ ወደብ ላይ እንደቆሙና ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት በሂደት ላይ እንዳሉ በማስመሰል ለተጎጂዎች ሐሰተኛ መረጃ መስጠታቸውን ፖሊስ ማረጋገጥ ችሏል።
በመስቀል አደባባይ ከተለያዩ ቦታዎች መኪኖችን በትውስት በማሰባሰብ ሕዝብን በሚያሳስት መልኩ ድርጅቱ ከውጭ ሀገር ያስገባቸው መኪኖች እንደሆኑ በማስመሰል እና የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ከሆነው ቢዋይዲ ከተባለ የቻይና ካምፓኒ ጋር ምንም ዓይነት ውል ሳይኖራቸው ውል እንዳላቸው አድርገው የማጭበርበር ወንጀል ሲፈጽሙ መቆየታቸውን ፖሊስ በምርመራ ደርሼበታለሁ ብሏል።
ተጠርጣሪዎቹ በጅቡቲ ውስጥ አልፋቲዞ በሚል ስም ድርጅት በማቋቋም BYD ከተባለ የቻይና ካምፓኒ ጋር አብሮ ከሚሰራ ሌላ ድርጅት ጋር በመነጋገር 10 ፐርሰንት ቅድመ ክፍያ በመክፈል የመጀመሪያዎቹን 148 መኪኖች ወደ ሀገር ውስጥ አስገብተው እንደነበርና ተጨማሪ 188 መኪኖችን በተመሳሳይ 10 ፐርሰንት ቅድመ ክፍያ ለድርጅቱ በመክፈል መኪኖቹን ተረክበው ወደ ሀገር ውስጥ ሳያስገቡ ጅቡቲ ላይ እንዲሸጡ ማድረጋቸውንና በአጠቃላይ 336 መኪኖችን 10 ፐርሰንት ጅቡቲ ለሚገኘው የቻይና ድርጅት በመክፈል ወስደው ቀሪ 90 ፐርሰንት ክፍያ አለመፈፀማቸውን ፌደራል ፖሊስ ባደረገው ምርመራ ደርሶበታል።
ከ1 ሺህ 200 በላይ ተጎጂዎችን በማጭበርበር መዝግበው 95 ሺህ ብር ቅድመ ክፍያ 285 ሺህ ብር የመንግስት ታክስ እንዲሁም 130 ሺህ ብር ለኤክትሪክ መኪና ቻርጀር ለማሰራትና ለባለሙያ በሚል ከእያንዳንዳቸው 1 ሚሊየን 365 ሺህ ብር መቀበላቸውን ፖሊስ አረጋግጧል፡፡
የፊንቴክ ኢንቨስትመንት ድርጅትን ባልተገባና በተጋነነ መልኩ በማስተዋወቅ በህገወጥ መንገድ ከተሰበሰበው ገንዘብ ተጋሪ በመሆን የተጠረጠሩ ሰለሞን ቦጋለ፣ ሰራዊት ፍቅሬ፣ ዳንኤል ተገኝ፣ አብርሃም ግዛው፣ ይገረም ደጀኔ፣ መንሱር ጀማል እና ካሊድ ናስር የተባሉ ታዋቂ አርቲስቶችና የማስታወቂያ ባለሙያዎችንም ፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎ ፍርድ ቤት በማቅረብ የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸው ፍርድ ቤትም እስከ መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም መፍቀዱ ተገልጿል፡፡
ፌደራል ፖሊስ በማጭበርበርና በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ (Money laundering) እና የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ጨምሮ በ19 የወንጀል ጉዳዮች በተጠረጠሩ የፊንቴክ ኢንቨስትመንት ድርጅት መስራቾችና ባለቤቶች እንዲሁም በሕብረተሰቡ ዘንድ ያላቸውን ዕውቅናና ተቀባይነት በመጠቀም ሆነ ብለው የተጋነነ ማስታወቂያ በመንገር እና በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ የሀሰት መረጃዎችን ለሕብረተሰቡ በማሰራጨት ዜጎችን እንዲጭበረበሩ በማድረግ በሕገወጥ መንገድ ከተገኘው ገንዘብ እያንዳንዳቸው አሁን ባለው የገበያ ዋጋ 8 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ቢ.ዋይ.ዲ ሶንግ ፕላስ የመኪና ስጦታ በመቀበል፤ በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ እና በዜጎች ላይ ከ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ በተጠረጠሩ አርቲስቶችና የማስታወቂያ ባለሙያዎች ላይ የጀመረውን ምርመራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ይህ ውስብስብ የወንጀል ጉዳይ በተሳካ ሁኔታ ተጣርቶ ክስ እንዲመሠረት ከፖሊስ ጋር በትብብር ለሠራው የፍትህ ሚኒስቴር እና በጉዳዩ ላይ መረጃ ሲሰጥ ለነበረው ሕብረተሰብ የፌደራል ፖሊስ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ ምስጋና አቅርቧል።