በህገወጥ የነዳጅ ነጋዴዎች ላይ የተቀናጀና ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል – ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በህገወጥ የነዳጅ ነጋዴዎች ላይ የተቀናጀና ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል አሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በክልሉ በየደረጃው ከሚገኙ አመራሮች ጋር የተወያዩ ሲሆን፥ ውይይቱ በዋናነት ከነዳጅ ጋር የተያያዙ ስጋቶችን ለመለየትና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለመቀየስ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
በነዳጅ እጥረት የሚከሰቱ ችግሮችን ለመሻገር ዜጎችና የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች በቁጠባና ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ብቻ መጠቀም እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ከነዳጅ እጥረት ጋር በተያያዘ ባቀረቡት የመወያያ ሰነድ በመካከለኛው ምስራቅ የተከሰተው ግጭት በነዳጅ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጫና ማስከተሉን አመልክተዋል፡፡
በክልሉ የነዳጅ ንግድ እንቅስቃሴ ላይ የተቀናጀ ቁጥጥር እንደሚደረግ ገልጸው፥ በህገወጥ የነዳጅ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ ርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የስራ ኃላፊዎች መሳተፋቸውን የርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት የዲጂታል ቴክኖሎጂና ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡