Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በቤት ልማት እና ተግዳሮት ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት እያካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የ50ኛ ዓመት ምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በቤት ልማት እና ተግዳሮት ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት እያካሄደ ነው።

ኮርፖሬሽኑ የ50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል በተለያዩ መርሐ ግብሮች እያከበረ ሲሆን÷ በዛሬው ዕለትም “የትናንት፣ ዛሬና የነገ ጉዞ ማሳያ እውነታዎች” በሚል መሪ ሐሳብ የተቋሙን ጉዞ የሚያመላክት የፓናል ውይይት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እያካሄደ ይገኛል።

በፓናል ውይይቱ ላይ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል (ዶ/ር) በቀድሞ መጠሪያው የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት የተቋቋመለትን ዓላማ ስቶ ወደ መውደቅ የተቃረበ ተቋም እንደነበር አስታውሰዋል።

ተቋሙ በ35 ሺህ ቤቶች ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመው÷ የነበሩ ሀብቶችን መረጃ የማደራጀትና የማስተዳደር ክፍተቶች በስፋት እንደነበሩ አመላክተዋል።

ይህንንም ታሪክ ለመቀየር የቀድሞውን የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ወደ ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በመቀየር ከስያሜ እስከ ተግባር የደረሰ ሪፎርም ተደርጓል ነው ያሉት።

በዚህም ኮርፖሬሽኑ ከ28 ዓመታት ወዲህ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታን በመጀመር በአጭር ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቁ መኖሪያ ቤቶችን አስመርቋል ብለዋል።

በተጨማሪም እንደ 3ዲ ያሉ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር የተሳለጡ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው÷ ኮርፖሬሽኑ ያቋቋመው የግንባታ ግብዓት ማምረቻ ተቋምም ከለውጡ ትሩፋቶች መካከል መሆኑን ተናግረዋል።

በሔብሮን ዋልታው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.