Fana: At a Speed of Life!

የነዳጅ ጥገኝነት ለመቀነስ ታዳሽ ኃይልን መጠቀም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የነዳጅ ጥገኝነት ለመቀነስ እና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የታዳሽ ኃይልን መጠቀም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው አለ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴዔታ ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ ምክንያት የተፈጠረው ችግር በነዳጅ ጥገኝነት ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ግንባታ አዋጭነትን ጥያቄ ውስጥ ከትቷል።

የነዳጅ ዘይት ጥገኝነትን ለመቀነስ የታዳሽ ኃይል ልማት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸው፤ የነዳጅ ዋጋ በየጊዜው መጨመር እና ለማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱ ታዳሽ ኃይል ላይ ለመስራት ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።

እንደ ሀገር ከነዳጅ ባሻገር ሌሎች የታዳሽ ኃይል አማራጮችን በመጠቀም ሀገር ለነዳጅ የምታወጣውን ወጪ መቀነስ ለኢኮኖሚው መነቃቃት ያለው ሚና ላቅ ያለ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

በመሆኑም አማራጭ የታዳሽ ኃይል ምንጮችን እና የተፈጥሮ ጸጋዎቻችንን መጠቀም እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ከአማራጭ የታዳሽ ኃይል ምንጮች መካከል ሶላር አንዱ መሆኑን አንስተው፤ እንደ ሀገር የታዳሽ ኃይልን ለመጠቀም የሚያስችለውን መመሪያ ወደ ተግባር ለማስገባት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በከተሞች የሶላር ኃይልን ጥቅም ላይ ማዋል በከፍተኛ ደረጃ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለመቆጠብ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር 100 ኪሎ ዋት ፒክ የሚያመነጭ የሶላር ፓርኪንግ ገንብቶ የሶላር ኃይል መጠቀም መጀመሩን አንስተው፤ የተቋማትና የህብረተሰቡን የታዳሽ ኃይል አጠቃቀምን ከማጠናከር ጎን ለጎን ስለ ታዳሽ ኃይል ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.