Fana: At a Speed of Life!

የቻይና ፋይናንስ ተቋማት ለቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የተመራ ልዑክ በቻይና ከሚገኙ የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል፡፡

አቶ አህመድ ሺዴን ጨምሮ የብሔራዊ ባክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ አመራሮች እና በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበውን ያካተተው ልዑኩ ከቻይና ኤግዚም ባንክ፣ ከቻይና ኢንዱስትሪና ንግድ ባንክ እንዲሁም ከቻይና ልማት ባንክ ስራ ኃላፊዎች ጋር ነው የተወያየው፡፡

ጉብኝቱ በሂደት ላይ የሚገኘውን የእዳ ሽግሽግን በተመለከተ ውይይት ማድረግን ጨምሮ ለግዙፉ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የገንዘብ አማራጮችን ለመፈለግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ በእዳ ሽግሽግ ላይ የተደረገው ውይይት አመርቂ ውጤት ያስገኘ መሆኑን ጠቅሰው÷ መንግስት የሚያስበውን የኢኮኖሚ እድገት መሬት ማውረድ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ሁለቱ ሀገራት ያላቸው ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በማስረዳት የቻይና ፋይናንስ ተቋማት ለቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የቻይና የፋይናንስ ተቋማት በበኩላቸው÷ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራርነት ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ለተገኘው አዎንታዊ ውጤት አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል፡፡

ሁለቱ ወገኖች ኢትዮጵያ እና ቻይና በፋይናንስ መሰረተ ልማቶች ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት በሚያጠናክሩበት ሁኔታ ላይ ከስምምነት መድረሳቸው ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.