42 በመቶ የሚሆነውን የህክምና ግብአት በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን ተችሏል – ዶ/ር መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገር ውስጥ የሚመረተውን የህክምና ግብአት ከ8 ወደ 42 በመቶ ማሳደግ ተችሏል አሉ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ።
ሚኒስትሯ 2ኛውን የሕክምና ምርቶች ማኑፋክቸሪንግ ኤግዚቢሽንና 10ኛውን ኢትዮ ኸልዝ አውደ ርዕይ በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት፥ ከውጭ የሚገቡ የህክምና ግብአቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
ከ25 በላይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በመድኃኒትና በሕክምና ግብአት ምርት በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አጠቃላይ የጤና ወጪ 127 ነጥብ 47 ቢሊየን ብር ደርሷል ያሉት ሚኒስትሯ፥ ይህም ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 6 ነጥብ 3 በመቶውን እንደሚይዝ አመልክተዋል፡፡
በሀገር ውስጥ የሚመረተው የህክምና የግብአቶች ምርት ከ8 ወደ በ42 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ገልጸው፥ ይህም በየዓመቱ ከ53 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ጫናን መቀነሱን አስረድተዋል።
አውደ ርዕዩ በጤና እንክብካቤ፣ በህከምና መገልገያዎች፣ በመድሃኒት የእሴት ሰንሰለትና በዲጂታል የጤና ስርዓት ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን፥ ከ90 በላይ በላይ ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ፡፡
በተጨማሪም የሀገር ውስጥ መድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎች አምራቾችን አቅም ለማሳየትና የገበያ ትስስርን ለመፍጠር እንዲሁም የዘርፍን ስትራቴጂያዊ ግቦች ይፋ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በሰዓዳ ጌታቸው