ኢራን የአሜሪካ ኤፍ -15 ተዋጊ ጄትን መትታ ጣለች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢራን ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የአሜሪካ ኤፍ-15 ተዋጊ ጄትን መትታ መጣሏ ተሰማ፡፡
አናዶሎ እንደዘገበው÷ ከአንድ ወር በላይ በቆየው ጦርነት የአሜሪካ ኤፍ -15 ተዋጊ ጄት በደቡባዊ ኢራን ተመትቶ ወድቋል፡፡
ከአደጋው በኋላ የነፍስ አድን ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን፤ በጄቱ ውስጥ ከነበሩ ሁለት አብራሪዎች ውስጥ አንደኛው በህይወት መትረፉ ሲገለፅ ሁለተኛው አብራሪ ግን ያለበት ሁኔታ አለመታወቁ ነው የተገለጸው፡፡
ቀደም ሲል የኢራን መንግሥት ሚዲያ የሆነው ፕሬስ ቲቪ የኢራን ወታደራዊ ሀይሎች “ስትራይክ ኤግል” የተባለውን የአሜሪካ ኤፍ -15 ተወጊ ጄት መትተው መጣላቸውን በምስል አስድግፎ ዘገባውን አውጥቶ ነበር፡፡
ከጉዳዩ ጋር የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት (ፔንታጎን) ምንም አይነት ምላሽ ሳይሰጥ የቆየ ቢሆንም ቢቢሲ እና ሌሎች መገናኛ ብዙኃኖች አረጋገጥን ባሉት ምስል ባለቤትነቱ የአሜሪካ የሆነ ኤፍ -15 ተዋጊ ጄት ተመትቶ መውደቁ ተረጋግጧል፡፡
ጥቃቱ የተፈጸመው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ተዋጊ ጄቶች ያለምንም ከልካይ በኢራን ሰማይ ስር እየተርመሰመሱ ነው፤ ኢራን ምንም ማድረግ አትችልም ሲሉ በተናገሩ ማግስት ነው፡፡
በሚኪያስ አየለ