የፌደራል እና ክልል መንግሥታት ግንኙነት እያጠናከረ ያለው አዋጅ …
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ዘሐራ ሁመድ የፌደራል እና ክልል መንግሥታት ግንኙነት ስርዓት አዋጅ በየዕርከኖች ያሉ ግንኙነቶችን አጠናክሯል አሉ።
የፌደሬሽን ምክር ቤት የደቡብ ኢትዮጵያ እና አጎራባች ክልሎች የመንግሥታት ግንኙነት መድረክ የፌደራልና የክልል ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሀዋሳ ከተማ እያካሄደ ነው።
መድረኩ በመንግሥታት መካከል ያሉ የጋራ ጉዳዮችን በአጋርነትና በትብብር ላይ የተመሰረተ የአመራር መርህ በመከተል በጋራ የሚመሩበትንና የሚመክሩበትን ስርዓት መገንባት ዋነኛ ዓላማው ነው።
ምክትል አፈ-ጉባዔዋ በመድረኩ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ዋስትና ያለው ዘላቂ ዴሞክራሲ ለማስቀጠል ከተናጠል ይልቅ በየዕርከኖች ያሉ ግንኙነቶችን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል።
ኢትዮጵያ የጉዳዩ አስፈላጊነት በማመን የፌደራል እና ክልል መንግሥታት ግንኙነት ስርዓት አዋጅ አውጥታ እየተገበረች እንደሆነ አስታውሰው፤ በአዋጁ መተግበር በክልሎች የጎንዮሽ ግንኙነትን ህዝብን ተጠቃሚ ያደረገ ውጤት መምጣቱን ጠቅሰዋል።
በክልሎች ህዝቦች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን መፍታት፣ በመሰረተ ልማት ማስተሳሰር፣ የህዝቦችን ግንኙነትን በማጠናከር ረገድ አዋጁ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ በአብነት አንስተዋል።
በመቅደስ አስፋው