Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓመት ከ20 ሚሊየን በላይ መንገደኞችን እያጓጓዘ ይገኛል – አቶ መስፍን ጣሰው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ150 በላይ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በመያዝ በዓመት ከ20 ሚሊየን በላይ መንገደኞችን እያጓጓዘ ይገኛል አሉ የአየር መንገዱ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው የኢትዮጵያ አየር መንገድ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ÷ አየር መንገዱ ያለፉትን 80 ዓመታት በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥ በማለፍና ፈተናዎችን በብልሃት በመወጣት ዛሬ ለደረሰበት ስኬት በቅቷል ብለዋል።

በቀጣይም ካለፉት ዓመታት በመማር እስከ ፈረንጆቹ 2040 የሚደርስ የረጅም ጊዜ እቅድ በማውጣት አየር መንገዱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

አየር መንገዱ አሁን ላይ 145 የዓለም አቀፍ እንዲሁም 23 የሀገር ውስጥ መዳረሻዎች እንዳሉት ገልጸው÷ ከ150 በላይ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በመያዝ በዓመት ከ20 ሚሊየን በላይ መንገደኞችን እያጓጓዘ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም ከአፍሪካ ቀደሚው አየር መንገድ መሆን መቻሉን አመላክተዋል።

አየር መንገዱ በፈረንጆቹ 2040 መዳረሻዎቹን ወደ 243፣ አውሮፕላኖቹን ወደ 350፣ የሚያጓጉዘውን ጭነት አሁን ካለበት በዓመት 850 ሺህ ቶን ወደ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ቶን እንዲሁም መንገደኞችን በዓመት ወደ 60 ሚሊየን ለማሳደግ እና ዓመታዊ ገቢውንም 30 ቢሊየን ዶላር ለማድረስ እንደሚሰራ አብራርተዋል።

ተቋሙ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዕድገት ለማፋጠን የበኩሉን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የአየር መንገዱን 80ኛ ዓመት በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ላይ መሆኑንና በቀጣይ 6 ሳምንታት በተለያዩ መርሐ ግብሮች እንደሚያከብርም ተናግረዋል።

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.