Fana: At a Speed of Life!

የኃያላንና ተቀናቃኝ ሀገራት መናኸሪያ የሆነችው ጂቡቲ…

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ጂቡቲ ከጎረቤቶቿ በተለየ የዓለም ኃያላንና ተቀናቃኝ ሀገራት የጦር ሰፈር የገነቡባት ሀገር ናት፡፡

ዘ ኢኮኖሚስት መጽሄት በሚያዝያ ወር እትሙ ÷ ሁሉም የዓለም ኃያላንና ተቀናቃኝ ሀገራት በጂቡቲ ትንሽ መሬት ይፈልጋሉ ሲል አስነብቧል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ ኃያላን ሀገራት እና መካከለኛ ሃይል ያላቸው ሀገራት ጂቡቲን የወታደራዊ ማዕከል እና የንግድ ስትራቴጂክ ሥፍራ እያደረጓት እንደሚገኙ አመልክቷል፡፡

ከ1 ሚሊየን በታች የሕዝብ ቁጥር ያላት ጂቡቲ ምንም አይነት ለም የተፈጥሮ ሀብት ባይኖራትም ስትራቴጂካዊ አቀማመጧ ግን የኃያላን ሀገራት መናኸሪያ እንድትሆን አስችሏታል፡፡

አሁን ላይም የዓለም ኃያላኖቹ አሜሪካ፣ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ጃፓን፣ ቱርክ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና ጣሊያንን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ለንግድ እና ለወታደራዊ ዓላማ የጦር ሰፈራቸውን በጅቡቲ ገንብተዋል፡፡

👉 ጂቡቲ ለምን የኃያላኑ ምርጫ ሆነች? ባለፉት ሰባት እና ስምንት ዓመታት ውስጥ የጅቡቲ ተፈላጊነት እየጨመረ የመጣ ሲሆን÷ ይህም ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ እድገት አዲስ እድል ይዞ መጥቷል፡፡

ሀገሪቱ በነዳጅ ሀብት የበለፀጉ የመካከለኛው ምስራቅ የዓረብ ሀገራትን እና አፍሪካን ታስተሳስራለች፤ ከየመን በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ መሆኑ ደግሞ የሰላጤው የንግድ መስመር መተላለፊያ እንድትሆን አድርጓታል፡፡

ይህም ቀይ ባሕርን እና ሕንድ ውቅያኖስን በማገናኘት በቀላሉ መርከቦች በሜድትራኒያን ባሕር በኩል ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ ለመመላለስ እንዲችሉ አይነተኛ ሚና ካለው የባብል መንደብ ወሽመጥ በቅርብ ርቀት እንድትገኛ አስችሏታል።

ይህ ስትራቴጂካዊ አቀማመጧም ከዓለማችን በመርከብ ከሚመላለስ ሸቀጥ 20 በመቶ እና 10 በመቶ ለዓለም ገበያ የሚቀርብ ነዳጅ የሚያልፍበትን ቀጣና ለመቆጣጠር በሚፈልግ ማንኛውም ሀገር ተመራጭ ያደርጋታል።

👉 ኢትዮጵያና ጅቡቲ ሁለቱ ሀገራት ባለፉት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ ያስመዘገበችውን ፈጣን እድገት ተከትሎ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው የበለጠ እየተጠናከረ መጥቷል፡፡

ኢኮኖሚያዊ እድገቱን ተከትሎ በወደብ ኪራይ እና ተጠቃሚነት ብቻ ታጥሮ የነበረው የሁለቱ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በታላላቅ የጋራ መሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተሳሰረ ይገኛል፡፡

ሀገራቱ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣በባቡር እና ወደብ ግንባታ ዘርፎች በትብብር እየሰሩ ሲሆን÷በአሁኑ ወቅት የገነቧቸው እና እየገነቧቸው የሚገኙ ፕሮጀክቶች የገንዘብ መጠን 10 ቢሊየን ዶላር ደርሷል።

የኢትዮጵያን 90 በመቶ ወጪ እና ገቢ ምርት ከሚያስተናግደው የጂቡቲ ወደብ የተሻለ ቅርበት የሚኖረው የሶስቱ ሀገራት (ጀቡቲ፣ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን) ፕሮጀክት የሆነው ታጁራ ወደብን ጨምሮ ከ9 ቢሊየን ዶላር በላይ የተበጀተላቸው ሌሎች ፕሮጀክቶች ግንባታን እያከናወኑ እንደሚገኙም ዘገባው አመልክቷል፡፡

ከኢኮኖሚያዊ ትብብሮች በተጨማሪ ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ በወታደራዊ ሃይል፣በቀጣናዊ ሰላም እና ጸጥታ እንዲሁም በሌሎች አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ትብብሮች በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.