ኢራን በሊባኖስ ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ከቀጠለ ከተኩስ አቁም ስምምነቱ እራሴን አገላለሁ አለች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢራን እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ የምትቀጥል ከሆነ ከተኩስ አቁም ስምምነቱ እራሷን እንደምታገል አስታውቃለች፡፡
ስሙ ያልተጠቀሰ የኢራን ከፍተኛ ባለስልጣን እንዳለው÷ እስራኤል በሊባኖስ ላይ እየፈጸመች ላለው ወታደራዊ ጥቃት ከኢራን አጸፋዊ ምላሽ ይጠብቃታል፡፡
እስራኤል በዛሬው ዕለት በሊባኖስ ላይ ጥቃት መፈጸሟ የተገለጸ ሲሆን÷ ይህም በአሜሪካ እና ኢራን መካካል የተደረሰውን የሁለት ሳምንታት የተኩስ አቁም ስምምነት ዘላቂነት ጥያቄ ውስጥ ከትቶታል፡፡
ኢራን ስምምነቱ መጣሱን በመጥቀስ ከተኩስ አቁም ስምምነቱ እራሷን ልታገል እንደምትችል እየገለጸች መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በአንጻሩ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነቱ አካል እንዳልሆነች ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ የሊባኖስ ጉዳይ በሂዝቦላህ ምክንያት በተኩስ አቁም ስምምነቱ ውስጥ ሳይካተት መቅረቱን አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል የፋርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው አሁን ላይ ነዳጅ የጫኑ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል እንዳያልፉ ተከልክለዋል፡፡
ክልከላው የተጣለውም እስራኤል ሊባኖስ ላይ የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ ሳይሆን እንዳልቀረ ነው የተመላከተው፡፡
በአቤል ነዋይ