Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አደጋ ስጋት አይበገሬነት እየሰራች ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሽግግርን ከአካባቢ ጥበቃና አደጋ መከላከል አቅም ግንባታ ጋር አስማምታ በመተግበር ለአፍሪካ አደጋ ስጋት አይበገሬነት እየሰራች ነው አሉ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው 16ኛው የአፍሪካ አደጋ ስጋት አቅም የባለድርሻ አካላት ጉባኤ ላይ ነው።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት መዛባት የሚያስከትለውን ዋጋ ትረዳለች፤ ተጽዕኖውንም አይታለች፤ ለለውጥም እየሰራች ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የኢትዮጵያ የልማት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ አህጉራዊ አጀንዳዎችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በአየር ንብረት ስማርት ግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና ቴክኖሎጂ ላይ ኢንቨስት እየተደረገ መሆኑንና የመቋቋም አቅምን በብሔራዊ ልማት ውስጥ እየተቀናጀ እንደሆነ ተናግረዋል።

ለአብነትም የአረንጓዴ አሻራ፣ የምግብ ሉዓላዊነት ንቅናቄ፣ የኮሪደር ልማት እና የታዳሽ ኃይል መስፋፋት ብሔራዊ ፕሮግራሞች ብቻ ሳይሆኑ አህጉራዊ የአደጋ መቋቋም አቅምን ለመገንባት፣ ራስን ለመቻልና ለማጠናከር እንዲሁም ዘላቂ መጻኢ እድልን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ የሩቅ ስጋት መሆኑ አብቅቶ በየዕለት ሕይወት እና ኑሮ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጸው÷ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ አውሎ ነፋስ፣ ወረርሽኝ እና የመሬት መንሸራተት እየተደጋገሙና እየጠነከሩ መጥተዋል ነው ያሉት።

ይህም ኢኮኖሚን በማናወጥ የምግብ ስርዓትን እንደሚያዳክሙና በሕዝብ ላይ የሚያሳድሩት ጫና ቀላል የሚባል እንዳልሆነ አስረድተዋል።

አፍሪካ ልታሳካው የምትችለውን ነገር የአፍሪካ አደጋ ስጋት አቅም እንደ ሞዴል ሆኖ ሊቆም ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ከአጀንዳ 2063 መንፈስ ጋር በሚናበብ መልኩም የአደጋ ስጋትን በራስ አቅም የምትቋቋም፣ በራሷ የምትተማመን እና የተዋሃደች አፍሪካ እውን ለማድረግ እንደ የአፍሪካ አደጋ ስጋት አቅም ያሉ ተቋማትን ማጠናከር ወደ ራዕያችን ያደርሰናል ብለዋል።

በለይኩን ዓለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.