ቅዳሜ ስዑር…
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዛሬዋ ዕለት ከወትሮ በተለየ መልኩ የኢየሱስን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረች ቅዳሜ ትባላለች።
ቀዳሚት ሰንበት “ቅዳሜ፣ ቀዳሚት ሰንበት” እየተባለች ትጠራለች፡፡ በዘመነ ብሉይ እግዚአብሔር ሕገ ኦሪትን ለሙሴ በሰጠበት ወቅት ከአስርቱ ቃላት አንዷ “የአምላክህን የእግዚአብሔርን ሰንበት አክብር፤ ስድስቱን ቀን ሥራህን ሥራ፣ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ ሰባተኛይቱ ቀን ግን ለእግዚአብሔር አምላክ ናት” በማለት ሰንበት ብሎ ራሱ እግዚአብሔር ሰይሟታል፡፡
ቅዳሜ ስዑር የተባለችበትም ዋና ምክንያት የፊተኛው ዕለተ ቀዳም እግዚአብሔር ፍጥረታትን ፈጥሮ ከሥራው ያረፈበት ዕለት እንደሆነ ሁሉ፤ አሁን ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራውን በመስቀል ላይ ፈጽሞ በከርሰ መቃብር ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ስላደረ ያ ቀን በአክፍሎት የሚዋልበትና የሚጾምበት በመሆኑ በሰንበት መጾም የማይገባ ሆኖ ሳለ ቅዳሜ ስዑር በመጾሙ “ቅዳሜ ስዑር” ተብላለች፡፡
“ስዑር” መባሏ በዓመት አንድ ጊዜ ስለምትጾም ነው፡፡ ሐዋርያት እህል እንቅመስ ባሉ ጊዜ ከመካከላቸው ያዕቆብ የተባለ ሐዋርያ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሦስተኛው ቀን እነሣለሁ ብሎ ነግሮናል የእርሱን መነሣት ሳላይ አልቀምስም አለ (ማር ፲፬÷፳፯—፳፱)፡፡
ሌሎችም ሐዋርያት እርሱን አብነት አድርገው ጌታችን በሦስተኛው ቀን እሑድ ሌሊት እስኪነሣ ድረስ እህል ሳይቀምሱ ቆይተዋል፡፡
ከዕለተ ዓርብ ጀምሮ እስከ እሑድ መንፈቀ ሌሊት ድረስ ከእህል ከውሃ ተከልክለው አክፍለዋል፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ ሠለስቱ ምዕትም በፍትሕ መንፈሳዊ “ዓርብንና ቅዳሜን አንድ አድርጋችሁ ጹሟቸው እስከ እሑድ ዶሮ ጩኸት ድረስ ምንም አይቀመስባቸውም፤ ሁለቱን ቀን መጾም የማይችል ግን ቀዳሚትን ብቻ ይጹም መድኃኒታችን በመቃብር አድሮባታልና” ሲሉ ፋሲካ እሑድ ዋዜማ ቅዳሜን መጾም እንደሚገባ ሥርዓት ሠርተዋል፡፡ (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭፤ ቁጥር ፭፻፸፯)፡፡
ስለዚህም በመጾም የተሻረች ዕለት ለማለት “ቅዳሜ ስዑር” በመባል ትጠራለች፡፡
ከቅዱሳን ሐዋርያት ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው ትውፊት መሠረት ቅዱሳን ሐዋርያት በማዘን፣ በመጾምና በመጸለይ ዕለቷን እንዳከበሯት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የተቻላቸው ከዓርብ ጀምረው የሚጾሙ ለሁለት ቀን እህል ውሃ ሳይቀምሱ ያድራሉ፤ ያልተቻላቸው ደግሞ ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡