በፓኪስታን የአሜሪካ እና ኢራን ድርድር ላይ የተነሱ የውይይት ነጥቦች
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መላው ዓለም በከፍተኛ ትኩረት ይጠብቀው የነበረው የአሜሪካና ኢራን የሰላም ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁ ይታወቃል።
የአሜሪካ እና የኢራን ባለስልጣናት በፓኪስታን ኢስላማባድ በትናንትናው ዕለት ተሰብስበው በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ጦርነት ለማስቆም ውይይት አድርገዋል፡፡
ቴህራን መደበኛ ውይይቶች ሊጀመሩ የሚችሉት ዋሽንግተን በሊባኖስ የተኩስ አቁም ቃል ከገባች እና በኢራን ላይ የተጣለው ማዕቀብ ከተነሳ በኋላ እንደሆነ ገልፃለች።
በፓኪስታን የአሜሪካ እና ኢራን ድርድር ላይ በርካታ ዋና ዋና የውይይት ነጥቦች ተነስተዋል፡፡
ኢራን በሊባኖስ ውስጥ የተኩስ አቁም እንዲኖር ሀሳብ ያቀረበች ሲሆን፥ እስራኤል እና አሜሪካ የሊባኖስ ዘመቻ የኢራን አሜሪካ አካል አይደለም ብለዋል፡፡
ኢራን በሆርሙዝ የባህር ዳርቻ ላይ ያላትን ሥልጣን እውቅና ማግኘት ትፈልጋለች፤ ይህም የመተላለፊያ ክፍያዎችን ለመሰብሰብ እና በአካባቢው ኃይል ውስጥ ትልቅ ለውጥ በሚያመጣ ሁኔታ ተደራሽነትን ለመቆጣጠር ዓላማ ያደረገችበት ነው።
ኢራን ለስድስት ሳምንታት በዘለቀው ጦርነት ለደረሰው ጉዳት ካሳ የምትፈልግ ሲሆን፥ አሜሪካ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት አልሰጠችም።
ኢራን ዩራኒየም ማበልጸግ ትፈልጋለች፤ ይህንን ሀሳብ ዋሽንግተን ውድቅ ያደረገች ሲሆን፥ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለድርድር የማይቀርብ ነው ብለዋል።
እስራኤል እና አሜሪካ የኢራን ሚሳኤል አቅም እንዲቀንስ ሀሳብ አቅርበዋል፤ ቴህራን አስፈሪው የሚሳኤል መሳሪያዋ ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን ገልጻለች።
ኢራን የአሜሪካ ተዋጊ ኃይሎች ከአካባቢው ለቀው እንዲወጡ እና በሁሉም ግንባሮች ጦርነት እንዲቆም ቁርጠኝነትን እንደምትፈልግ ማሳወቋን ሬውተርስ ዘግቧል፡፡
ትራምፕ የሰላም ስምምነት እስኪደረስ ድረስ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ወታደራዊ ሃብቶችን ለማቆየት ቃል የገቡ ሲሆን፥ ይህን ማክበር ካልቻሉ ጦርነቱ ከፍተኛ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።
በወንድማገኝ ጸጋዬ