አሜሪካ ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገቡና የሚወጡ መርከቦችን ማገድ ጀመረች
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ የባሕር ላይ ጉዞዎችን ማገድ መጀመሯን አስታውቃለች፡፡
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ኢራን ወደቦች የሚገቡና የሚወጡ መርከቦች ላይ በዛሬው ዕለት ክልከላ እንደሚጥሉ ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡
በዚህ መሰረትም አሁን ላይ አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች አሊያም ከኢራን ወደቦች ወደ ሌላ ቦታ የሚደረጉ የባሕር ላይ ጉዞዎችን ማገድ መጀመሯን ሲኤን ኤን ዘግቧል፡፡
እገዳው አሜሪካና ኢራን የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነትን ለማስቆም በፓኪስታን ያካሄዱት የፊት ለፊት የሰላም ውይይት ያለስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ የተላለፈ ነው፡፡
ክልከላው ኢራን የዓለም ቁልፍ የነዳጅ መተላለፊያ መስመር የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ እንድትከፍት ጫና ለማሳደር ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የአሜሪካ ጦር ክልከላውን በመተላለፍ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ወደ ኢራን ወደቦች የሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ ርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡
ለዚህም አሁን ላይ የአሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚን ጨምሮ ሦስት የጦር መርከቦች በኦማን ባሕረ ሰላጤ አቅራቢያ መሰማራታቸው ነው የተገለጸው፡፡
የኢራን ጦር በበኩሉ በሀገሪቱ ወደቦች በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ጥቃት ቀጣናውን ከፍተኛ ችግር ውስጥ ሊከት ይችላል ሲል አስጠንቅቋል፡፡
በሆርሙዝ ወሽመጥ የቴህራን ጠላቶችና እና አጋሮች መርከቦች ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ እንደማይፈቅድም አስገንዝቧል፡፡
የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ሞሃመድ ባጋር ጋሊቢፍ ቀደም ሲል እንዳሉት÷ቴህራን አሜሪካ በየጊዜው በምታስተላልፈው የትኛውም ዛቻ እና ማስፈራሪያ እጅ አትሰጥም፡፡
አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ማገድ መጀመሯም ቋፍ ላይ የሚገኘውን የመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና ይበልጥ ሊያባብሰው እንደሚችል በዘገባው ተመላክቷል፡፡
የዋሽንግተንና ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ ውዝግብን ተክትሎም የዓለም የነዳጅ ዋጋ በድጋሚ በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ አሻቅቧል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል የሆርሙዝ ወሽመጥ በአሜሪካ መዘጋትን ስትደግፍ በአንጻሩ ዩናይትድ ኪንግደም ክልከላውን ተቃውማለች፡፡
በመላኩ ገድፍ