Fana: At a Speed of Life!

የእስራኤል እና ሊባኖስ የፊት ለፊት ውይይት ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እስራኤል እና ሊባኖስ ከሶስት አስርት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያደርጉት የፊት ለፊት ዲፕሎማሲያዊ ውይይት ዛሬ ምሽት በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ይካሄዳል፡፡

ውይይቱ በእስራኤል እና ሂዝቦላህ መካከል ለወራት ከተካሄደው አስከፊ ጦርነት በኋላ የሚደረግ ሲሆን÷ ጦርነቱን ሊያስቆም እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

እስራኤል እና ሊባኖስ በሚዋሰኑበት ሰሜናዊ ድንበር ላይ ያለውን ሰላም ለማረጋገጥ እና ጦርነቱን በዘላቂነት ለማስቆም ያለመውን ውይይት ለማካሄድ ተወካዮቹ ዋሽንግተን መድረሳቸውን የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንትን ጠቅሶ አረብ ኒውስ ዘግቧል፡፡

በውይይቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፣ በአሜሪካ የእስራኤል አምባሳደር ይኼል ሌይተር እና በአሜሪካ የሊባኖስ አምባሳደር ናዳ ሀምዳህ መዋድ ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡

ኢራን ከአሜሪካ ጋር በምታደርገው ውይይት ላይ የእስራኤል እና ሂዝቦላህን ጉዳይ በድርድር ነጥቦች ቢካተትም ሊባኖስ ግን ራሷን ችላ ከእስራኤል ጋር እየተነጋገረች መሆኑ ተሰምቷል፡፡

ይሁን እንጂ በሊባኖስ ባለስልጣናት ላይ እምነት እንደሌለው የሚገልጸው ሂዝቦላህ ከእስራኤል ጋር የገባበትን ጦርነት በተመለከተ የኢራን አቋም እንዲጠበቅለት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ተገልጿል፡፡

ሂዝቦላህ የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ከተከፈተ ከሳምንታት በኋላ በሰሜናዊ እስራኤል የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃት በመፈፀም ጦርነቱን መቀላቀሉ ተመላክቷል፡፡

እስራኤልም የቡድኑን ወታደራዊ አቅም ለማዳከም የአየር ጥቃት እና የምድር ላይ ዘመቻ በመጀመሯ 166 ሕጻናትን ጨምር ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች ለሕልፈት ተዳርገዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.