ኢራን የሆርሙዝ ሰርጥን ዳግም ዘጋች
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢራን የሆርሙዝ ሰርጥን ዳግም መዝጋቷን አስታወቀች።
በትናንትናው ዕለት ኢራን በሊባኖስ እና እስራኤል መካከል የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ የሆርሙዝ ሰርጥ ለንግድ መርከቦች ሙሉ በሙሉ ክፍት እንዲሆን ወስና የነበረ ቢሆንም በዛሬው ዕለት ዳግም ዝግ ማድረጓን ገልጻለች።
የሀገሪቱ የጦር ኃይል የሆርሙዝ ሰርጥ በድጋሚ መዘጋቱን የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙሃን የዘገቡ ሲሆን፤ ይህንንም ተከትሎ በዓለም አቀፍ የንግድ መርከቦች ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል እየታየ ነው።
ይህንንም ተከትሎ ሚነርቫ ኤቭሮፒ የተባለችውን የንግድ መርከብ ጨምሮ በባህር መስመሩ ላይ የነበሩ በርካታ መርከቦች ጉዟቸውን እያቋረጡና ወደ መጡበት አቅጣጭ እየተመለሱ እንደሆነ የዘገበው ቢቢሲ ነው።
በሌላ በኩል በሊባኖስ የተደረሰው ተኩስ አቁም ስምምነት በአብዛኛው እየተከበረ ቢሆንም የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ በአንድ ሞተር ሳይክል ላይ በፈጸመው ጥቃት የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን ሊባኖስ ገልጻለች።
እስራኤል ጥቃቱ የተፈጸመው ሊሰነዘር የነበረን ጥቃት ለመከላከል እንደሆነ መግለጿም ተነግሯል።
በሶስና አለማየሁ