በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት።
የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ጎበዜ አበራ እንዳሉት÷ በክልሉ ካሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመቀናጀት ሰላማዊ፣ ተዓማኒ፣ ግልጽ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ በርካታ ተግባራት እየተከናወነ ነው።
ሀገራዊና ብሔራዊ ጥቅምን በማስቀደም በሕዝብ ይሁንታ የተመረጠ ፓርቲ እንዲኖር የማስተማርና ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው÷ ከምርጫ ባሻገር ስለሀገር ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል።
ምክር ቤቱ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠትና ሰላምን ለማጽናት በቅንጅት የተለያዩ ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ፓርቲዎች የምርጫ መተዳደሪያ ደንብ በመጠበቅ የየራሳቸውን ሐሳብና ማንፌስቶ እያስተዋወቁ እንደሆነ አንስተው÷ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም ምርጫ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በማቴዎስ ፈለቀ