Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት የስራ ቡድን ስብሰባ በጄኔቫ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት 7ኛ የስራ ቡድን ስብሰባ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ በይፋ መካሄድ ጀምሯል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር እና ዋና ተደራዳሪ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በስብሰባው መክፈቻ ላይ፤ የኢትዮጵያን የአባልነት ጉዞ ለማፋጠን የስራ ቡድን ስብሰባ ሊቀመንበር፣ ሴክሬተሪያትና አባላት ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።

ባለፈው መስከረም ወር ከተካሄደው 6ኛው የስራ ቡድን ስብሰባ ወዲህ ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገንና በሁለትዮሽ ድርድሮች ከፍተኛ እመርታ ማሳየቷን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለ226 አባል ሀገራት ጥያቄዎች ጥልቅ ምላሾችን የመስጠት፣ የስራ ቡድን ረቂቅ ሪፖርትን የማዳበርና 32 የግዴታ አንቀጾችን የማጠናቀቅ ስራ ማከናወኗን ተናግረዋል።

ከ9 አባላት ጋር የሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ድርድሮችን ማጠናቀቋን ጠቅሰው፤ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከአባላት የተነሱ ወሳኝ ቀሪ ጉዳዮችን ለማከናወን ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ በሁሉን አቀፍ ማክሮኢኮኖሚ ሪፎርም ለሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን መፍጠሯን ጠቁመዋል።

ለባለብዙ ወገን ዓለም አቀፍ የንግድ ስርዓት ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኗን መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.