በፌደራል ደረጃ 1 ነጥብ 1 ትሪሊየን ብር ገቢ ተሰብስቧል – ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሤ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሤ በዘንድሮው በጀት አመት 9 ወራት በፌደራል መንግስት ደረጃ 1 ነጥብ 1 ትሪሊየን ብር ገቢ ተሰብስቧል አሉ።
የ2018 በጀት ዓመት ሦስተኛው የ100 ቀናት እና የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።
የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሤ የአፈጻጸም ግምገማውን ተከትሎ በገቢ አሰባሰብ ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች እንደ ሀገር የገቢ አቅም ተሻሽሏል ብለዋል።
ከዚህ በፊት ለሀገር የሚገባው ገቢ ዝቅተኛ እንደነበረና ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ያህል ገቢ ተሰብስቦ ለዜጎች የልማት ፍላጎት ከማዋል አኳያ ሰፊ ጉድለት እንደነበረ ተናግረዋል።
አክለውም በቀደሙት ጊዜያት እንደ ሀገር በጠቅላላው የሚሰበሰበው ገቢ ከ100 ቢሊየኖች ያልተሻገረ እንደነበር አስታውሰው፥ አሁን ላይ ግን ከገቢ አንጻር መሻሻል መታየቱን አመልክተዋል።
በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በፌደራል ደረጃ 1 ነጥብ 1 ትሪሊየን ብር መሰብሰቡን ገልጸው፥ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ 1 ነጥብ 5 ትሪሊየን ብር ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በተመሳሳይ ወቅት እንደ ሀገር ደግሞ ከ1 ነጥብ 5 ትሪሊየን በላይ ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል ያሉት ሚኒስትሯ፥ የመካከለኛ ዘመን የገቢ ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ስራ መገባቱንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ብዙ መልማት የሚገባቸው ፕሮጀክቶች ያሏት በመሆኑ ያንን ሊመጥን የሚችልና የበጀት ጉድለትን ለማጥበብ የሀገር ውስጥ የገቢ አቅምን ለማሻሻል እየተሰራ ነው ብለዋል።
በሶስና አለማየሁ