ለደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ማያርዲት አሸኛኘት ተደረገላቸው
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ማያርዲት አሸኛኘት አድርገዋል።
ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ማያርዲት ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ትናንት አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ ቆይታቸውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በተለያዩ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ማያርዲት ጋር ቀጣናውን መልክ በሚያሲዙ እና የጋራ መፃኢ የልማት ጉዳዮች ላይ የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው መግለጻቸው ይታወሳል።
በዚሁም የሁለቱ ሀገራት የላቀ እድገትና ተጠቃሚነት ዙሪያ መረጃ መለዋወጣቸውን ገልጸው÷ የኢኮኖሚ ትስስርን በጠንካራ ትብብር እና በኢንቨስትመንት በመደገፍ እድሎችን ማስፋት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ምክክር ማድረጋቸውን አመልክተዋል።
በለይኩን ዓለም