Fana: At a Speed of Life!

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወተው የድንች ምርታማነት…

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻልና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት በተመረጡ የሰብል ዓይነቶች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።
ለዚህም ትልቁ ማሳያ በስንዴ ምርት ላይ የተገኘው ውጤት ሲሆን÷ ኢትዮጵያ ስንዴን ከውጭ ከማስገባት አምርቶ ለውጭ ገበያ እስከ ማቅረብ የደረሰ ስኬት ማምጣቷ ለበርካታ ሀገራት ተምሳሌት እንድትሆን አስችሏታል።
ከስንዴ ባሻገር በሌሎች የሰብል ዓይነቶች ላይ የተለያዩ ሥራዎች በመስራት በተለይም ከስንዴ ያልተናነሰ አቅም ያለው እና የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ ዋና የግብርና ስትራቴጂካዊ ሰብል ተብለው ከተመረጡት መካከል የሆነው ድንች ላይ መስራት ወሳኝ ነው።
በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሆለታ ምርምር ማዕከል የድንች ተመራማሪ የሆኑት አጸደ ሰለሞን ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ድንች የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለኢንዱስትሪ ሽግግርና ለውጭ ምንዛሪ ምንጭነትም ቁልፍ ሚና መጫወት የሚችል ሰብል ነው።
ከደቡብ አሜሪካ አንዲያን ተራራማ ቦታዎች የተገኘው ድንች ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በአውሮፓ መተዋወቁን አንስተው÷ በትንሽ መሬት ላይ ብዙ ካሎሪ ያለውን ምርት በመስጠት በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ከረሃብ መታደጉን ተናግረዋል።
በወቅቱ በአውሮፓ በነበረው የሕዝብ ቁጥር መጨመርና የምግብ እጥረት ድንች ዋና ምግብ መሆን የቻለ ሰብል ሲሆን÷ በተለይም ለአየርላንድ እና ለጀርመን ሕዝቦች ዋነኛ ምግብ በመሆን ለኢኮኖሚ እድገታቸው መሰረት ጥሏል።
ድንች ወደ ኢትዮጵያ የገባው በፈረንጆቹ 1858 በጀርመናዊው ሳይንቲስት ሺምፐር አማካኝነት እንደሆነ እና መጀመሪያ አካባቢ እንደ ጓሮ አትክልት ብቻ ይታይ እንደነበር ያነሱት ተመራማሪዋ÷ ዛሬ ላይ ከ456 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ይመረታል ተብሎ እንደሚገመት ያስረዳሉ።
ድንች ከሌሎች የእህል ሰብሎች በበለጠ ፍጥነት የሚደርስ፣ በትንሽ ቦታ ብዙ ምርት የሚሰጥና ከተለያዩ የአየር ንብረት ሁኔታዎች ጋር ቶሎ መላመድ የሚችል እንደሆነ በመግለጽ÷ ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የምግብ እጥረት በሚያጋጥምበት ወቅት ድንች በ90 ቀናት ውስጥ በመድረስ ፈጣን መፍትሔ እንደሚሆን አስረድተዋል።
ድንች ከሌሎች የእህል ሰብሎች ጋር ሲነጻጸር በአንድ ሄክታር መሬት ላይ እስከ 400 ኩንታል ምርት መስጠት በመቻል ከፍተኛ የምርታማነት አቅም እንዳለው አብራርተዋል።
የድንች ምርትን ለማሳደግም ከ50 ዓመታት በፊት ጀምሮ የምርምር ሥራዎች በተለያዩ የምርምር ማዕከላት በስፋት እየተሰሩ እንደሚገኙ በመጥቀስ በሽታን የሚቋቋሙ፣ ምርታማነታቸው ከፍተኛ የሆኑና ለኢንዱስትሪ ተስማሚ የሆኑ ዝርያዎችን ማውጣት ላይ ትኩረት ያደረጉ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።
በዚህም ከኢትዮጵያ ሥነ ምህዳር ጋር ተስማሚ የሆነ ዘር በማላመድ ረገድ ትልቅ ስራ መሰራቱን ጠቅሰው÷ ይህም በአማካይ በዓመት ከ4 ነጥብ 3 ሚሊየን ቶን በላይ የድንች ምርት እንዲመረት አስችሏል ብለዋል።
ድንች በሚፈለገው መልኩ እንዳይመረት ጥራት ያለው ዘር እጥረት ዋናው ችግር መሆኑን ያነሱት ተመራማሪዋ÷ የዳበረ የዘር ሥርዓት አለመኖሩ ዝርያዎችን ለበሽታ ስርጭት ተጋላጭ እንዲሆኑ እንደሚያደርጋቸው ጠቁመዋል።
በገበያ ሰንሰለቱ ላይ የሚስተዋለው ችግር ሌላኛው ማነቆ እንደሆነና በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ድንች በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ጎረቤት ሀገራት ሱዳን፣ ጅቡቲና ኬንያ እንደሚላክ ገልጸው÷ ይህም ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ትክክለኛ የውጭ ምንዛሪ እንዳታገኝ ያደርጋታል ነው ያሉት።
በመሆኑም የድንች ዘር ሥርዓትን ሕጋዊና ዘመናዊ በማድረግ፣ ምርቱን መከታተል የሚያስችል አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ይህም ጥራት ያለውን ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ እና ለሀገር ውስጥ ፍጆታም ማሟላት እንደሚያስችል ጠቁመው÷ ባለድርሻ አካላት በተቀናጀ መንገድ መሥራት እንደሚገባቸው አመላክተዋል።
እሴት በመጨመር ድንችን ወደ ዱቄት፣ ቺፕስና ሌሎች ምርቶች የሚቀይሩ ፋብሪካዎችን ማስፋፋት ምርት እንዳይበላሽና ገበሬው የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ እንደሚረዳም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ያስመዘገበችው ስኬት በድንች ላይም ሊደገም ይገባል የሚሉት ተመራማሪዋ÷ በትንሽ ጊዜና መሬት የሚገኘው ከፍተኛ ምርት ለምግብ ሉዓላዊነት ጉዟችን ትልቅ አቅም የመሆን፣ የሥራ እድል የመፍጠር እና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የመሆን አቅም እንዳለው ጠቁመዋል።
በዮናስ ጌትነት
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.