Fana: At a Speed of Life!

የአቅም ውስንነት ያለባቸውን ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰራር..

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የገንዘብ ውስንነት ያለባቸው አዲስ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ ፈላጊ ደንበኞች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር ዘርግቻለሁ አለ።

የአገልግሎቱ የማርኬቲንግ ሽያጭ እና ደንበኞች አገልግሎት ስራ አስፈጻሚ ኢሳያስ ደንድር በሰጡት መግለጫ÷ የአቅም ውስንነት ያለባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በሁለት ዓመት የጊዜ ገደብ መክፈል የሚያስችላቸውን ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

የተዘረጋው አዲስ አሰራር መደበኛውን ወይም ነጠላ ፌዝ ቆጣሪ ለሚፈልጉ አዲስ ደንበኞች ብቻ አንደሆነ ገልጸዋል።

አገልግሎቱ ባደረገው ጥናት በከተሞች ከአቅም ውስንነት ጋር ተያይዞ ቆጣሪ ማስገባት ያልቻሉ ዜጎች መኖራቸወን ማረጋገጡን ገልጸው÷ ይህንን ታሳቢ በማድረግ በአንድ ጊዜ መክፈል የማይችሉ ዜጎች እስከ 6 ወር ያለምንም ወለድ አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉበት አሰራር ተዘጋጅቷል ነው ያሉት።

አሰራሩም ደንበኞች ከ6 አስከ 12 ወራት 3 በመቶ ወለድ ፣ ከ12 አስከ 18 ወራት 6 በመቶ ወለድ እንዲሁም ከ18 እስከ 24 ወር 9 በመቶ ወለድ በመክፈል አገልግሎቱን እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት ከግማሽ ሚሊየን በላይ አዳዲስ ቆጣሪዎችን የማገናኘት ስራ መሰራቱን አንስተው÷ በዚህ ዓመትም ከ800 ሺህ በላይ አዳዲስ ቆጣሪዎችን ለማስገባት እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።

በቅድስት ብርሃኑ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.