የአርሶ እና አርብቶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ ለመለወጥ ያለመው የገጠር ኮሪደር ልማት
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት ኢትዮጵያን የሚመጥን ከተማን ለመገንባት የኮሪደር ልማቱን ከአዲስ አበባ በመጀመር በሁሉም ክልል ከተሞች የማልማት ስራ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
የኮሪደር ልማት ከከተሞች ዕድገት ጋር የተሳሰረና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፍትሃዊ ልማት ለዜጎች ለማቅረብ በማለም በትኩረት እየተሰራ ያለ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክት ነው፡፡
በዚሁም መንግሥት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚኖረው ገጠር በመሆኑ የዜጎችን ህይወት ለመቀየርና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በከተሞች በተሰራው የኮሪደር ልማት የታየውን አመርቂ ውጤት በገጠርም ለመድገም አቅጣጫ በማስቀመጥ ወደ ስራ መግባቱ የሚታወስ ነው።
ለዚህም በከተማ ብቻ ሳይገደብ የገጠሩን ማህበረሰብ አኗኗር ለማሻሻል የገጠር ኮሪደር ልማት ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
የገጠር ኮሪደር ልማትን ተግባራዊ ማድረግ የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን ፍልሰት በመቀነስ የተመጣጠነ ዕድገትን ለማምጣት ወሳኝ እንደሆነ ታምኖበት ወደ ተግባር የገባ ፕሮጀክት ነው፡፡
ይህም የተስተካከለ ኑሮንና ከተሜነትን ወደ ገጠር በማምጣት ሞዴል የገጠር መንደሮች ቀላል ወጪ የሚጠይቁና በአካባቢው በሚገኙ ግብዓቶች የሚገነቡ እንዲሁም አርሶ አደሩ ጤናማና ክብር ያለውን ህይወት እንዲኖር የሚያስችል የልማት አካል ነው።
የገጠር ኮሪደር ልማት ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ስነ ምህዳራዊ ፋይዳን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ሲሆን÷ ይህም ዘላቂ ልማትና የተረጋጋ ኅብረተሰብ ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ታምኖበታል።
ከለውጡ በፊት የኢኮኖሚ ምንጭ የሆነው የገጠሩ አካባቢ ትኩረት ተነፍጎት ቢቆይም የለውጡ መንግሥት የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ወደ ከተማ የሚሄደውን አርሶ አደር በሚኖርበት ተረጋግቶ እሴት መጨመር ላይ እየሰራ እንዲኖር የሚያስችል ሁኔታ ፈጥሯል።
የገጠር ኮሪደር አጠቃላይ የሕብረተሰብ ሽግግርን የሚያመጣና መሰረተ ልማትን ጨምሮ የተለያዩ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ጉዳዮችን ያቀፈ ሲሆን÷ በገጠር አካባቢዎች ዘመናዊ አኗኗርን የሚፈጥርና የአርሶ አደሩን ህይወት የሚቀይርም ነው።
የገጠር ኮሪደር ልማት አርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚና ዘመናዊ ስልተ ምርት እንዲከተል በማድረግ ባህሉን እና ወጉን ጠብቆ አካባቢውን ንጹህ፣ ጓሮውን በዶሮ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ እንዲሁም በማርና ወተት ምርት የተትረፈረፈ በማድረግ ቀላል የአኗኗር ስልት እንዲከተል ያደርጋል፡፡
በአድማሱ አራጋው