Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ማዕድን ዘርፍ አዲስ ገፅታ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ያላትን ግዙፍ አቅም ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ስኬት ለመቀየር በጀመረችው ሪፎርም የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅር እየቀየረ የሚገኝ አዲስ ተስፋ ሆኖ ብቅ ብሏል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በመንግሥት የተወሰዱ ስር ነቀል የፖሊሲ ርምጃዎች እና የማክሮኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ዘርፉን ከነበረበት የልማዳዊ አሰራር እና የኮንትሮባንድ ሰንሰለት በማላቀቅ የሀገራዊ እድገቱ ዋነኛ ሞተር እንዲሆን አስችለውታል።
እንደሚታወቀው ቀደም ባሉት ጊዜያት የኢትዮጵያ ማዕድን ዘርፍ በተለይም የወርቅ ምርት በብዛት በባህላዊ አምራቾች ላይ በመመስረቱ፣ በኮንትሮባንድና በህገ ወጥ ዝውውር በመታጠሩ የሚያመጣው የውጭ ምንዛሪ መጠን እጅግ አነስተኛ ነበር።
ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት የነበረው ድርሻም ከ1 በመቶ በታች ሆኖ ዘልቋል።
የሀገራዊ ለውጡ እውን መሆንን ተከትሎ መንግሥት ዘርፉን ከግብርና በመቀጠል የኢኮኖሚው ስትራቴጂካዊ ምሰሶ አድርጎ በመቅረጹ ስር ነቀል ለውጦች ታይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የማዕድን ሀብቷ የተከበረች ሀገር እንደሚያደርጋትና ዘርፉ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትን ለማሟላት ወሳኝ መሆኑን መናገራቸው አይዘነጋም።
ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ እያከናወነችው ያለው ሪፎርም በቁጥር የተደገፉ ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል።
ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ከ2010 እስከ 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ለውጭ ገበያ የቀረበው የወርቅ ምርት የ1 ሺህ 241 ነጥብ 4 በመቶ እድገት ማስመዝገቡ ነው።
በተመሳሳይ የድንጋይ ከሰል ምርትን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በተደረገው ጥረት በ2010 ዓ.ም 17 በመቶ ብቻ የነበረው የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻ በ2017 ዓ.ም ወደ 75 በመቶ ከፍ ብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ የመረቁት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን የሚገኘው የአርጆ የድንጋይ ከሰል ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በሰዓት እስከ 200 ቶን የማምረት አቅም አለው።
ከዚህም በተጨማሪ ወደ ስራ የገቡና በመግባት ላይ ያሉ ግዙፍ የማዕድን ፕሮጀክቶች ለዘርፉ ተስፋ ሰጪ ሆነዋል።
በወርቅ ዘርፍ እንደ የኤምጄ ማዕድን፣ የኢትኖ ማዕድን እና አዲሃ ማዕድን ያሉ ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ሲሆኑ፤ በ2017 በጀት ዓመት ብቻ የወርቅ ምርት ከነበረበት 3 ነጥብ 9 ቶን ወደ 39 ቶን በማደግ የ10 እጥፍ ጭማሪ በማስመዝገብ 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱ ለአብነት የሚጠቀስ ስኬት ነው።
በሲሚንቶ ምርት ደግሞ ለሚ ናሽናል ሲሚንቶን ጨምሮ የአዳዲስ ፋብሪካዎች ግንባታ ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ እያሸጋገሩት ሲሆን የሲሚንቶ ዓመታዊ ምርትም ወደ 20 ሚሊየን ቶን አድጓል።
ከእነዚህም ባሻገር እንደ ሴራሚክ፣ መስታወት፣ ብረት እና ግራፋይት ያሉ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች በሀገር ውስጥ በስፋት እንዲመረቱ በመደረጉ ዘርፉ የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ሽግግር በጽኑ መሰረት ላይ እንዲቆም እያደረገው ይገኛል።
በዘርፉ የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ስራ ሲጀምሩ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የማዕድን ዘርፍ ያላትን ተጽዕኖ ይበልጥ እንድታጠናክር ያደርጓታል።
በአጠቃላይ የማዕድን ዘርፍ በወጪ ንግድ ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ዕድገት በማሳየት እንዲሁም በሀገር ደረጃ ስትራቴጂክ የገቢ ምርቶችን በመተካት ለኢኮኖሚ ዕድገት ገንቢ አበርክቶ እያደረገ ነው።
በሶስና አለማየሁ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.