Fana: At a Speed of Life!

የማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር ስጋቱን ወደ መልካም አጋጣሚ ቀይሯል – አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር የነበረበትን ዘመናት ያስቆጠረ ስጋት በማስወገድ ወደ ላቀ የኢንቨስትመንት ምዕራፍ ተሸጋግሯል አሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ።

የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር በተለያዩ የሀገራችን ከተሞች ያስገነባቸውን ዘመናዊ ሕንፃዎች በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ይህንኑ አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ተቋሙ የነበረበትን ዘመናት ያስቆጠረ ስጋት በማስወገድ ወደ ላቀ የኢንቨስትመንት ምዕራፍ መሸጋገሩን ገልጸዋል።

ተቋሙ ላለፉት ሰባት አሥርተ ዓመታት የመንግሥት ሠራተኛው ዋስትና ሆኖ ቢቆይም የጡረታ ፈንዱን በአግባቡ የማንቀሳቀስ እና ወደ ኢንቨስትመንት የመቀየር አቅም ማጣቱ ለረጅም ጊዜ ስጋት ሆኖ ቆይቷልም ነው ያሉት።

ይሁን እንጂ የለውጡ መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት እና በወሰዳቸው የሪፎርም እርምጃዎች አዳዲስ አዋጆች እና የአስተዳደር ደንቦች እንዲጸድቁ ተደርጓል ብለዋል።

ይህም ተቋሙ የነበረበትን ስጋት ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ፈንዱን ከማስጠበቅ ባለፈ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሰማራ እና በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ማስቻሉን አመላክተዋል።

ዛሬ የተመረቁት ዘመናዊ ሕንፃዎች ከግዙፍ ቁሳዊ ሀብትነታቸው ባሻገር ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ፍሬ እና የነገው ብሩህ ተስፋ ማሳያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

መንግሥት ለተቋሙ የሚያደርገው ድጋፍ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል በመግባት ለስኬቱ አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና ማቅረባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.