Fana: At a Speed of Life!

103 አዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆኑ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት 103 አዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሆነዋል አለ፡፡

የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጌቱ ገረመው (ኢ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ፍትሃዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በተከናወነ ዘርፈ ብዙ ስራ ከዋናው ግሪድና ከግሪድ የራቁ በርካታ አዳዲስ አካባቢዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።

ከጤናና ማህበራዊ ተቋማት በተጨማሪ ከ31 ሺህ በላይ አባዎራዎችና እማዎራዎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲጠቀሙ አስችሏልም ነው ያሉት።

በዚህም በዘጠኝ ወራት ተጠቃሚ ከሆኑት ውስጥ 82ቱ ከዋናው የኤሌክትሪክ መረብ (ግሪድ) እንዲሁም 21 የገጠር ከተሞችና መንደሮችን ደግሞ በፀሐይ ኃይል አማራጭ (ኦፍግሪድ) የተገናኙ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ተደራሽነትን ከማረጋገጥ አኳያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 423 ሺህ 200 አዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

አፈፃፀሙም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ18 ነጥብ 6 በመቶ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል።

ኃይል ከተገናኘላቸው አዳዲስ ደንበኞች ውስጥ 31 ሺህ 298 ያህሉ አዲስ የኤሌክትሪክ ተደራሽ በሆኑት የገጠር ከተሞችና መንደሮች ተጠቃሚ የሆኑ ናቸው ብለዋል።

አዲስ ኤሌክትሪክ ካገኙ ደንበኞች መካከል 74 ነጥብ 2 ከመቶ የድህረ ክፍያ እንዲሁም 25 ነጥብ 8 በመቶ የቅድመ ክፍያ ቆጣሪ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ያለፉት ዘጠኝ ወራት አፈፃፀም ጨምሮ በአሁን ወቅት አጠቃላይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ ደንበኞች ቁጥር 5 ነጥብ 64 ሚሊየን መድረሱን ጌቱ (ኢ/ር) ተናግረዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.