Fana: At a Speed of Life!

ተጠናክሮ የቀጠለው የኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲ …

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች እያጠናከረች ትገኛለች፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና አንድነትን ከማስከበር፣ የኢኮኖሚ ልማትን ከማፋጠን እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ከመገንባት አንፃር በርካታ ስኬቶች እየተመዘገቡበት ይገኛል፡፡

ባለፉት ወራት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋር በመወያየት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን ማጠናከር የሚያስችሉ ምክክሮች አድርገዋል፡፡

በዚህ ወር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሞዛምቢክ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ዳንኤል ፍራንሲስኮ ቻፖ ጋር የተወያዩ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ በተለያዩ ዘርፎች ላይ በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ ስምምነቶችን ተፈራረመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተመሳሳይ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከነበሩት የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ጋር ውይይት በማድረግ የሁለትዮሽ ግንኙነቶች እና የወል የትብብር መስኮችን ለማጠናከር ያለመ ምክክር አድርገዋል፡፡

በተመሳሳይ ከቡሩንዲ ፕሬዚዳንት ኢቫሪስቴ ንድያይሺሚዬ እና የላይቤሪያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ንዩማ ቦአካይ ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን አድርገዋል፡፡

ከሀገራቱ መሪዎች ጋር ከነበራቸው ውጤታማ ውይይት በኋላ በተለያዩ ዘርፎች ያለውን ትብብር ለማጠናከር የሚያስችሉ ስምምነቶች ተፈርመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ እነዚህ ስምምነቶች ኢትዮጵያ በፈጣን የለውጥ ጉዞ ያካበተችውን ልምድ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለማካፈል፤ እንዲሁም ከአጋሮቻችን የተለያዩ ዕይታዎችን በመቅሰም ለአኅጉሩ ዕድገት ዘላቂና አፍሪካዊ መፍትሄዎችን በጋራ ለማፍለቅ እንደ ወሳኝ መሠረት ያገለግላሉ ብለዋል።

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.