Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካን 1 ነጥብ 3 ትሪሊየን ዶላር የዕዳ ጫና የሚቀንሱ መፍትሔዎችን ለማመላከት…

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አፍሪካ ያለባትን የ1 ነጥብ 3 ትሪሊየን ዶላር የዕዳ ጫና ለመቀነስ የሚያስችሉ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ 2ኛው የአፍሪካ የሉዓላዊ ፋይናንስ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

ፎረሙ 23 የአፍሪካ ሀገራት በከፍተኛ የዕዳ ቀውስ ውስጥ በሚገኙበት ወቅት በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አማካኝነት ነው የተዘጋጀው፡፡

የአፍሪካ ሀገራት በአሁኑ ወቅት ካላቸው ጠቅላላ ገቢ ውስጥ ከአንድ አራተኛ በላይ የሚሆነውን ለዕዳ ክፍያ አገልግሎት ለማዋል መገደዳቸው በመድረኩ ላይ ተመላክቷል።

ፎረሙ የአፍሪካን የፋይናንስ አስተዳደር ከተለመደው የዕዳ ክፍያ ማራዘም በማላቀቅ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙና ዘላቂ የፋይናንስ ስልቶችን ወደ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ማዕቀፎች ለማስገባት ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል።

የዕዳ ክፍያ ጫናው በብዙ ሀገራት ለጤና እና ለትምህርት ዘርፍ ከተመደበው ጠቅላላ በጀት እንደሚበልጥ የተገለጸ ሲሆን ÷ ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገትንና ኢንቨስትመንትን እየጎዳ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡

አፍሪካ ለዓለም አቀፍ የበካይ ጋዝ ልቀት የምታበረክተው አስተዋጽኦ ከ4 በመቶ በታች ቢሆንም ከዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ፋይናንስ የምታገኘው ድርሻ ግን 3 ነጥብ 5 በመቶ ነው፡፡

ስለሆነም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ተጋላጭነቶች የአፍሪካን የብድር አቅም እንዳያዳክሙ ተግባራዊ ስልቶችን መንደፍ እንደሚያስፈልግ ተመልክቷል፡፡

በጉባዔው ማጠናቀቂያ ላይ ተሳታፊ ሀገራት የየራሳቸውን የዕዳ አስተዳደር ሥርዓት ለማዘመን የሚያስችል የቴክኒክ ድጋፍና የተግባር መርሐ ግብር ያዘጋጃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአፍሪካን የጋራ የፋይናንስ እና የዕዳ ማሻሻያ ፍላጎት የሚያንጸባርቅ የአቋም መግለጫ በማውጣት ጉባዔው እንደሚጠናቀቅም ተጠቁሟል፡፡

በመሳፍንት ብርሌ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.