የአፍሪካን ትክክለኛ ታሪክ ለማስተዋወቅ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ትብብር አስፈላጊ ነው
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካን ትክክለኛ ታሪክ ለዓለም ለማስተዋወቅ የአህጉሪቱ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጠንካራ ትብብር አስፈላጊ ነው አሉ አፍሪካውያን የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች፡፡
“ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለተሻለች አፍሪካ” በሚል መሪ ሃሳብ የአፍሪካን ትክክለኛ ትርክት ለዓለም ለማስተዋወቅ ያለመ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች አህጉራዊ ጉባኤ ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
መድረኩን ፐልስ ኦፍ አፍሪካ ከኤ ጂ ኤ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን፥ የአህጉሪቷ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ዳያስፖራዎችና የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች የረጅም ጊዜ ትብብር የሚፈጥሩበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በጉባኤው ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ የገቡት ሴኔጋላዊው የይዘት ፈጣሪ ጃው ኬቹን እና ቤኒናዊቷ የዲጂታል ተፅዕኖ ፈጣሪ ሬጂ ቦይዘር መድረኩ ለግንኙነትና ለልምድ ልውውጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ጉባኤው የአፍሪካን የዲጂታል ድምፆች ለማቀራረብና የአፍሪካዊያንን የቴክኖሎጂ፣ ባህል፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎች ለዓለም ለማስተዋወቅ ድንበር ተሻጋሪ ፋይዳ እንዳለው ነው የገለጹት፡፡
በዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚካሄደው ጉባኤ አዲስ አበባን የአፍሪካን ዲጂታል የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚቀርጹ ውይይቶች ማዕከል እንደሚያደርጋት ኢዜአ ዘግቧል፡፡