Fana: At a Speed of Life!

ተመራማሪዎች የኢትዮጵያን ግብ በመረዳት ሊሰሩ ይገባል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተመራማሪዎች የኢትዮጵያን ፍላጎት፣ ግብ እና አካሄድ በመረዳት ሊሰሩ ይገባል አሉ።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ያዘጋጀው የፖሊሲ ቀን ”መረጃ ለልህቀት፤ የፖሊሲ ሚና ለበለጸገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሐሳብ ተካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ስኬታማ ሀገራት በመሠረተ ልማትና በኢንዱስትሪ ላይ ብቻ ሳይሆን በዕውቀት፣ በምርምርና በስትራቴጂያዊ አስተሳሰብ ላይ ጭምር ኢንቨስት የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።
ፖሊሲ ቀጣይ መንገድን የሚያመለክት መሆኑን አንስተው÷ የፖሊሲ አማካሪ ተቋማት በዕውቀትና በተግባር መካከል እንደ ድልድይ ሆነው እንደሚያገለግሉና የምርምር ውጤቶችን ወደ ፖሊሲ አማራጭነት በመለወጥ መረጃዎችን ከውሳኔ አሰጣጥ ጋር እንደሚያስተሳስሩ አስረድተዋል።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ሕዝብን በዕውቀት በመምራት በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለውን መተማመን በመገንባት ረገድ የማይናቅ ሚና አለውም ነው ያሉት።
ኢንስቲትዩቱ ምርጥ ምሁራን የሚሰባሰቡበት፣ ምርጥ ጥናቶች የሚታተሙበትና ምርጥ ሐሳቦች የሚፈልቁበት ማዕከል መሆን እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።
የመደመር መንግሥት ለሐሳብ እና ለዕሳቤ የተለየ ቦታ ያለው በመሆኑ ኢንስትቲዩቱ ሐሳብ ወደ ዕሳቤ የሚሻገርበት ሥፍራ እንዲሆን ይጠበቃል ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብልጽግና ጉዟችንን በማያቋርጥና ቀጣይነት ባለው የእውቀት ኢኮኖሚ ግንባታ እንዲሁም በጥናትና ምርምር ፅኑ መሰረት ለመገንባት እንሰራለን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በለይኩን ዓለም
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.