ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ስትራቴጂካዊ ምሰሶ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአሕጉራዊ ትስስርና ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ስትራቴጂካዊ ምሰሶ ነው አሉ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ ዓለም አቀፍ የባህል ቀን እና የቆመ የአውሮፕላን ዐውደ ርዕይ አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተለያዩ የባህል ትርኢቶችን ጨምሮ አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት ለአገልግሎት የሚጠቀምባቸው የአውሮፕላን ሞዴሎች ለጉብኝት ቀርበዋል።
ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በወቅቱ ባደረጉት ንግግር÷ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ስትራቴጂካዊ ምሰሶ ነው ብለዋል።
አየር መንገዱ የተባበሩት መንግሥታት ከተመሰረተ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ መመስረቱ ለታሪካዊ ቅርሱ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸው÷ ተቋሙ የአፍሪካ አቪዬሽን ተምሳሌት፣ የጥንካሬ፣ የራዕይ እና የሀገር ኩራት መሆኑን ተናግረዋል።
አየር መንገዱ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በአፍሪካ እና በሌሎች የዓለም ሀገራት እንደ ድልድይ ሆኖ በማገልገል ለቱሪዝም፣ ለዲፕሎማሲ፣ ለባህል ልውውጥ እና ለንግድ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አመልክተዋል።
በቀጣይ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናን ውጤታማ ለማድረግና ወደ አረንጓዴ ኃይል የሚደረገውን ሽግግር ለማፋጠን በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው÷ አየር መንገዱ የምስረታ በዓሉን ሲያከብር አዳዲስ መዳረሻዎችን ለማስፋፋት፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ለማጎልበት እና ዓለም አቀፍ አጋርነቱን ይበልጥ ለማጠናከር መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘመናዊ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂዎችን እና አውሮፕላኖችን በመጠቀም ረገድ ቀዳሚ መሆኑንና የዛሬው መርሐ ግብርም የተቋሙን ሰፊ ዓለም አቀፋዊ ተሳትፎ የሚያሳይ እንደሆነ አመልክተዋል።
የአየር መንገዱ የአውሮፕላን ስብስብ ለተቋሙ ቀጣይነት ያለው ዕድገትና ልማት ዋነኛ የጀርባ አጥንት በመሆኑ ከቦይንግ እና ኤርባስ ኩባንያዎች ከ100 በላይ አዳዲስ አውሮፕላኖችን ማዘዙን ገልጸው÷ ርክክቡም ከአሁኑ ጀምሮ እስከ ፈረንጆቹ 2031 ድረስ እንደሚከናወን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት በ147 አውሮፕላኖች በዓመት ከ21 ሚሊየን በላይ መንገደኞችን የሚያስተናግድ ሲሆን÷ በ5 አሕጉራት በሚገኙ ከ80 በላይ ሀገራት 140 መዳረሻዎች አሉት።
በመሳፍንት ብርሌ