ቡታጅራ ከተማ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንድትሆን በትኩረት መስራት ይገባል – እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ቡታጅራ ከተማ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንድትሆን በትኩረት መስራት ይገባል አሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)።
በከተማዋ ሲከናወኑ የቆዩ የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻ ማሻሻያ እና የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ሰጪ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት እንዳሻዉ ጣሰው (ዶ/ር)፤ ቡታጅራ ያላትን የቆየ የሰላም እሴት አድንቀዋል።
ከተማዋ ያላትን የውስጥ ገቢ አሟጥጣ በመጠቀም የልማት ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም እውን የማድረግ ተግባርን ልታጠናክር ይገባል ብለዋል፡፡
በብዝሃነት የደመቀችውን የቡታጅራ ከተማ የዘላቂ ሰላም ተምሳሌትነቷን ማጠናከር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከተማዋን ለመኖሪያ፣ ለንግድ እና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንድትሆን በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በዛሬው ዕለት በይፋ ከተመረቁት ፕሮጀክቶች ውስጥ የእሬንዛፍ ወንዝ ዳርቻ ልማት የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ እና የኮሪደር ልማት ስራዎች ይገኙበታል።
በተጨማሪም ከኮሪደር ልማቱ ጎን ለጎን የህብረተሰቡን የጤና ችግር የሚያቃልል ዘመናዊ የማህበረሰብ አቀፍ ፋርማሲ ተገንብቶ ለአገልግሎት በቅቷል።
በኦሊያድ በዳኔ