ኢትዮጵያን ወደ ነገ የሚያሻግር ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል – የመዲናዋ ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያን ወደ ነገ የሚያሻግር የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይከናወናል።
ከፋና ዲጂታል ጋር ቆይታ ያደረጉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት፥ በመጪው ምርጫ በንቃት ለመሳተፍ የመራጮች ካርድ አውጥተው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
ነዋሪዎቹ በፋና መድረክ እና በሌሎች የመገናኛ ብዙሃን አማራጮች የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸውን የፖሊሲ አማራጮችና ሀሳቦቻቸውን በመከታተል ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
መድረኩ ለሀገር ዕድገት ይበጃል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ እንዳገዛቸው ገልጸው፥ በምርጫው ዕለት በንቃት ለመሳተፍ ተዘጋጅተናል ነው ያሉት፡፡
ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲከናወን የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፥ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ወሳኝ መሆናቸውን በመገንዘብ በድምጽ መስጫው ዕለት በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ 47 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነትና በንቃት እየተሳተፉ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 10 ሺህ 934 ዕጩዎችን ማስመዝገብ ችለዋል።
ዜጎች ምርጫዬ የተሰኘውን ዘመናዊ የዲጂታል መተግበሪያ በመጠቀምና በምርጫ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት የምርጫ ካርዳቸውን ወስደዋል።
በሶስና አለማየሁ