የመደመር እሳቤን መሰረት ያደረገ የመረጃ ተኮር ፖሊሲ አመራርና ውሳኔ ሰጪነትን ማረጋገጥ ተችሏል – ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር እሳቤን መሰረት ያደረገ የመረጃ ተኮር ፖሊሲ አመራር እና ውሳኔ ሰጪነትን ማረጋገጥ ተችሏል አሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፡፡
”የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነፃነት” በሚል መሪ ቃል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የመረጃ ሉዓላዊነት ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በመድረኩ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ቀደም ሲል ሀገራዊ የመረጃ ሥርዓቱ በራስ አቅም ላይ ያልተመሠረተ፣ በውጭ ድጋፍ ጥገኝነት ላይ የቆየና የተዓማኒነት ጥያቄዎች የሚነሱበት እንደነበር አንስተዋል።
ከዚህ ለመላቀቅ በተደረጉ ቁርጠኛ ርምጃዎች የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርምና የ10 ዓመቱን የልማት ዕቅድ አፈጻጸም ለመከታተል የሚያስችሉ የተለያዩ የመረጃ ስርዓቶች ይፋ መደረጋቸውን ገልፀዋል፡፡
ለአብነትም የቤተሰብ ጥናት፣ የቱሪዝም መረጃ እና የቢዝነስ ድርጅቶች ቆጠራ ሥርዓቶች እንዲሁም የተለያዩ የዳሰሳ ጥናት በማድረግና በዲጂታል ሥርዓት በማዘመን ለመረጃ ልማት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም የመደመር እሳቤን መሠረት ያደረገ የመረጃ ተኮር ፖሊሲ አመራርና ውሳኔ ሰጪነትን ማረጋገጥ ተችሏል ነው ያሉት።
ይህ ዓይነቱ የሪፎርም ውጤት መረጃዎች በኢትዮጵያ ልጆች እንዲሰበሰቡና እንዲተነተኑ በማድረግ የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የፖሊሲ ነፃነት የሚያረጋግጥ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።
በተጨማሪም ብሔራዊ ጥቅምን፣ የዜጎችን ደኅንነትና የልማት ትልሞችን በጽኑ መሠረት ላይ በመገንባት ከተለመደው የምላሽ ሰጭነት አሠራር ወደ ቅድመ-ትንበያ መሸጋገር የሚያስችል ዘላቂ ተቋማዊ ዐቅም መፍጠሩ ተገልጿል፡፡