የኢትዮጵያ የመረጃ ሉዓላዊነት ጉዞ…
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሁን ወቅት ዓለም ላይ ሉዓላዊነት የሚደፈረው በድንበር ወረራ ብቻ ሳይሆን መረጃን በመመንተፍ ጭምር ነው።
ታዳጊ ሀገራት በመረጃ ቅኝ ግዛት ውስጥ እየወደቁ ባሉበት በዚህ ዘመን፤ የራስን መረጃ መቆጣጠርና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ ሆኗል።
ኢትዮጵያ የውጭ ተፅዕኖን በመስበር በዚህ ረገድ ቀድማ እየተራመደች ትገኛለች።
ከርምጃዎቿ መካከልም የሦስት ዓመት የስታቲስቲካል ልማት ፕሮግራም ቀርጻ እየተገበረች ሲሆን ፕሮግራሙ እንደ ሀገር መረጃ በማመንጨትና በመተንተን በኩል የነበረን የውጭ አካላት ተጽዕኖ አስቀርቷል፡፡
በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ በማካሄድ እንደ ሀገር 2 ነጥብ 6 ሚሊየን የኢኮኖሚ ድርጅቶች መኖራቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።
ከ23 ዓመታት በኋላ 92 በመቶ በአካል፣ 8 በመቶ ደግሞ በሪሞት ሴንሲንግ ቴክኖሎጂ የታገዘ የግብርና ቆጠራ መከናወኑም ተመላክቷል።
የዚህ ድምር ውጤት ኢትዮጵያ ከውጭ ተጽዕኖ ወጥታ በራሷ ሞዴሎች የኢኮኖሚ ትንበያ እንድትሰራ አስተማማኝ የፖሊሲ ግብዓት እንዲኖር ማስቻሉ ነው የተገለጸው፡፡
በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ የመረጃ ታማኝነትን ያሳደገ ሲሆን የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂም ሌላኛው ተጠቃሽ ስኬት ነው።
እነዚህ ስኬቶች የሚዳሰሱበት “የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነፃነት” በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀው ሃገራዊ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።