ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የከተሞች ፎረም ላይ እየተሳተፈች ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በባኩ አዘርባጃን እየተካሄደ በሚገኘው 13ኛው ዓለም አቀፍ የከተሞች ፎረም ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ቤት ለሁሉም፤ ደህንነታቸው የተጠበቀ እና ጠንካራ ከተሞች እና ማህበረሰቦች” በሚል መሪ ሐሳብ ፎረሙ እየተካሄደ እንደሆነ ገልጸዋል።
በፎረሙ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ልዑክ የኢትዮጵያን ብሎም የአዲስ አበባን ገፅታ ለዓለም ማስተዋወቅ የሚችል ሰፊ የስራ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ፎረሙ ዓለም አቀፋዊ የመኖሪያ ቤት ችግርን መፍታት፣ ዘላቂ የከተማ ልማት፣ ጠንካራ እና ሁሉን አቀፍ ከተሞች፣ የአየር ንብረትና የመኖሪያ ቤት ግንኙነቶች፣ መልሶ ግንባታ እና ተመጣጣኝ የመኖሪያ ቤት የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚመክር መሆኑን ጠቁመዋል።
የልምድ ልውውጥ እና የመስክ ጉብኝት እንደሚካሄድም ጠቅሰዋል።
መንግሥት ከግል ዘርፉ ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን የሚገልጽ ማራኪ ፓቪሊዮን (ቡዝ) በዛሬው ዕለት በተከፈተው ኤክስፖ ላይ አዘጋጅቷል።
በዚህም በተለያዩ መንገዶች የተዘጋጁ መረጃዎችን በጽሑፍ፣ በቪዲዮ እና በቨርቹዋል ሪያሊቲ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ሰፊ የማስተዋወቅ ሥራዎችን እየተሠራ ይገኛል።