በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ዜጎች ደህንነት እንዲጠበቅ እየተሰራ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ደህንነታቸው እንዲጠበቅ መንግሥት በቅርበት እየሰራ ነው አለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው በሰጡት መግለጫ÷ ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች ጋር ጠንካራና ንቁ ዲፕሎማሲያው ግንኙነትን ማድረጓን አንስተዋል፡፡
ለአብነትም ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ባደረገችው የሁለትዮሽ ውይይት መዋቅራዊ ስምምነት የጋራ ትግበራን የሚሹ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ በተባበሩት መንግስታት የምስረታ 80ኛ ዓመት በዓል ኢትዮጵያ መሳተፏን ጠቅሰው፤ ተሳትፎው ኢትዮጵያ ከድርጅቱ ጋር ያላትን ታሪካዊ ትስስር ያሳየችበት እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ላይ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ የገለፁት ቃል አቀባዩ÷ በደቡብ አፍሪካና ሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ልዑክ መቋቋሙን ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይ በህንድ ኒው ዴልሂ በተካሄደው የብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር ውጤታማ ውይይቶች ተደርገዋል ነው ያሉት፡፡
በቤተልሔም መኳንንት