ግብጽ የቀጣናው ሀገራት ልማት እንዳይሳካ ለዘመናት ትንኮሳ ስትፈጽም ቆይታለች – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ግብጽ የቀጣናው ሀገራት የመልማት ፍላጎት እንዳይሳካ የምትፈጽመው ትንኮሳ አዲስ ክስተት ሳይሆን ለዘመናት የተከተለችው ስልት ነው አለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ፥ ግብፅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች እንዳይከበሩ ጫና እያደረገች መሆኑን አንስተዋል፡፡
ግብፅ ቀጣናው ውጥረት ውስጥ እንዲገባ የሚያደርጉ የተለያዩ ትንኮሳዎችን በተደጋጋሚ ስትፈፅም መቆየቷን አስታውሰው፥ ይህ ትንኮሳ አዲስ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ ስትከተለው የቆየችው ስልት መሆኑን አስረደተዋል፡፡
በተለይም ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ማቅረቧን ተከትሎ ግብፅ ጥያቄውን ለማፈንና ትኩረት ለማሳጣት በርካታ ጫናዎችን ማድረጓን ቀጥላለች ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት አጀንዳዋን አጠናክራ ትቀጥላለች ያሉት ቃል አቀባዩ፥ ጥያቄው በተለያዩ መንግስታትና ተቋማት ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የባህር በር ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ መፈታት አለበት የሚል ጽኑ እምነት እንዳለው ገልጸው፥ ይህም ለተለያዩ ሀገራት መሪዎች መገለጹን አንስተዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ