የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እድገትን የሚደግፍ የትራንስፖርት ሥርዓት ለመገንባት እየተሰራ ነው – ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ የኢኮኖሚ እድገትን የሚደግፍ የትራንስፖርት ሥርዓት ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማስፋፋትና የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን የተዘጋጀ የብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ስትራቴጂና የትግበራ ማዕቀፍ ይፋ ተደርጓል።
ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ባለፉት ዓመታት አረንጓዴ፣ ጠንካራና ቀልጣፋ የትራንስፖርት ስርዓትን ለማጎልበት የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
የትራንስፖርት ዘርፉ ከኢኮኖሚ ጉዳይና የማህበራዊ ለውጥ ዋና ምሰሶዎች አንዱ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ለአካባቢ ተስማሚ የትራንስፖርት መፍትሄዎችን በማስተዋወቅ አበረታች እድገት መመዝገቡን አንስተዋል፡፡
ስትራቴጂው በመላ ሀገሪቱ የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴን ለማፋጠን አጠቃላይ ፍኖተ ካርታ የሚሰጥ ሲሆን፥ የፖሊሲ እና የቁጥጥር ስርዓት፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሁም የህዝብ ትራንስፖርት ኤሌክትሪፊኬሽንና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ እንደሚያካትት ተገልጿል፡፡
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ከማስተዋወቅ ባሻገር ዘመናዊ የትራንስፖርት ሥነ ምህዳርን መገንባት እንደሚያስችል ገልጸው፥ ለከተማ ፅዱነት፣ ለጤና፣ የኢነርጂ ደህንነትን ለማሻሻልና ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ትልቅ እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
የአፍሪካ ኅብረት የትራንስፖርትና ኢነርጂ ቴክኒካል ኮሚቴ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን አህጉራዊ ማዕቀፍ በቅርቡ ማፅደቁ አበረታች ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያ ለዚህ አህጉራዊ አጀንዳ ውጤታማነት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሥርዓትን እንደሚደግፍ ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረገው ስትራቴጂ የማምረቻ አካባቢ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ኢንቨስትመንትና የስራ ዕድል ፈጠራን ያበረታታል ነው ያሉት፡፡
በታምራት ደለሊ