የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ለዘላቂ የውሃ ሀብት ልማት …
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር እና የምርምር ስራዎች ለዘላቂ የውሃ ሀብት ልማት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተመላከተ።
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ልዩ አማካሪ ሚካኤል መሐሪ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በየዓመቱ የሚገኘው ዝናብ ከሶስት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ወደ ጎረቤት ሀገራት ይፈስሳል።
በመሆኑም የሀገሪቱ የውሃ ሀብት አስተዳደር በዋናነት ውሃን በቁጠባ እና በማጠራቀም ላይ ሊያተኩር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ለዚህም ሲባል ትናንሽ፣ መካከለኛ እና ትላልቅ ግድቦችን ጨምሮ የተለያዩ የውሃ ማቆር ስልቶችን እና የማጠራቀሚያ መሠረተ ልማቶችን በሰፊው ጥቅም ላይ ማዋል እንዲሁም ውሃው በማይኖርበት ወቅት በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አብዛኞቹ ተፋሰሶች ድንበር ተሻጋሪ መሆናቸው በዘርፉ ትልቅ ፈተና እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ፈተናውን ወደ ዕድል በመቀየር ውጤታማ የውሃ ዲፕሎማሲ ስራ በመስራት ብሔራዊ ጥቅምን ከማስጠበቅ ባለፈ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሰላምና ትብብርን ለመፍጠር አይነተኛ መንገድ መክፈት መቻሉን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የታችኞቹን ተፋሰስ ሀገራት በማይጎዳ፣ ፍትሃዊና ምክንያታዊ አጠቃቀምን በማረጋገጥ ዓለም አቀፍ መርሆዎች ላይ እንደተመሰረተ ተናግረዋል።
ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ቀጣይነት ያለው ውይይት እና ትብብር ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ታምሩ ተሰማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የውሃ ሀብትን በአግባቡ ማስተዳደር የመስኖ ልማትን ለማፋጠንና እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎችን ለመገንባት ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ንጹህ የመጠጥ ውሃ ላላገኘው የህብረተሰብ ክፍል ከጉድጓድና ከምንጮች የውሃ አቅርቦትን በማጎልበት ተደራሽነቱን በፍጥነት ማረጋገጥ የወቅቱ አንኳር ተግባር መሆኑን አንስተዋል።
ለዚህም ዘመኑን የዋጁና የሀገርን ጥቅም የሚያስከብሩ የምርምር ስራዎች ወሳኝ ናቸው ብለዋል።
የውሃ ሀብትን በጋራ ማልማት የአፍሪካን አንድነትና ትስስር ለማጠናከር ትልቅ አቅም እንዳለው የገለጹት ደግሞ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዚዳንት ተክሉ ወጋየሁ (ዶ/ር) ናቸው።
የተፋሰሱን ሀገራት የሚያስተሳስረው ዋነኛ ሰንሰለት ውሃ በመሆኑ፣ የተቀናጀ የውሃ አስተዳደርን በመተግበር የተሻለችና ብሩህ ተስፋ ያላት አፍሪካን መፍጠር እንደሚቻል አስረድተዋል።
በዮናስ ጌትነት