ኢትዮ ቴሌኮም በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ተመዘገበ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ላይ በይፋ ተመዝግቧል፡፡
በዚህም መሰረት የኢትዮ ቴሌኮም ባለአክሲዮኖች አክሲዮናቸውን በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ላይ መግዛት፣ መሸጥና ማስተላለፍ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ÷ ኩባንያው ለሕዝብ ይፋ ካደረገው የ10 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ሽያጭ ውስጥ አክሲዮኖችን ወደ ዲጂታል የመቀየር ሂደታቸውን ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
በዚህም 45 ሺህ በላይ ባለ አክሲዮኖች ግብይት መፈፀም እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡
ባለአክሲዮኖች ይህንን ግብይት መጀመር የሚችሉት በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ፈቃድ ከተሰጣቸው አገበያዮች ወይም የኢንቨስትመንት ባንኮች ዘንድ በመቅረብ የንግድ አካውንት ሲከፍቱ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል በብሔራዊ መታወቂያ መረጃ አለመሟላት ምክንያትና ያልተረጋገጡ 1 ሺህ 646 ባለአክሲዮኖች መረጃዎቻቸውን በአፋጣኝ እንዲያሟሉ ኩባንያው ጥሪ አቅርቧል::
እንዲሁም የኢትዮ ቴሌኮም አክስዮኖችን ለመግዛት የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን የማያሟሉ የአክሲዮን ግዢ ጥያቄ አቅራቢ 248 የውጭ ዜጎች የገዟቸውን 105 ሺህ አክሲዮኖች የከፈሉት ገንዘብ ተረጋግጦ ተመላሽ ይደረጋል ተብሏል።
በመቅደስ የኔሁን