በሐጅ ሥነ ሥርዓት ላይ የሚከናወነው ጀመራት …
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሐጅ ሥነ ሥርዓት ላይ ከሚከናወኑ ታላላቅ እና ጉልህ መንፈሳዊ ተግባራት አንዱ የጀመራት የጠጠር ውርወራ (የጀመራት ሥነ ሥርዓት) ነው።
ይህ ተግባር በሚና ሸለቆ ውስጥ በሚገኙ ሶስት ተለዋዋጭ የድንጋይ ምሰሶዎች (ጀመራቱል አቅባ፣ ጀመራቱል ውስጣ እና ጀመራቱል ሱግራ) ላይ ጠጠር በመወርወር ይፈጸማል።
ይህ ተግባር ነቢዩ ኢብራሂም (ዐ.ሰ) የአላህን ትዕዛዝ ለመፈጸም ልጃቸውን ኢስማኢልን ለመሰዋት ሲሄዱ ሰይጣን በተደጋጋሚ ሊያሳስታቸው በሞከረ ጊዜ ድንጋይ በመወርወር ያባረሩበትን ታሪካዊ ሁነት ያስታውሳል።
በመሆኑም ጠጠር መወርወሩ የሰይጣንን ክፉ ሀሳብ እና የእራስን የውስጥ ፍላጎት (ነፍስን) የማሸነፍ ምሳሌያዊ መግለጫ ነው።
ሥነ ሥርዓቱ የሚጀምረው በዒድ አል አድሃ (የአረፋ በዓል) መጀመሪያ ቀን ሲሆን በዕለቱ ትልቁ ምሰሶ (ጀመራቱል አቅባ) ላይ ሰባት ጠጠሮች ይወረወራሉ።
በቀጣዮቹ ከዙልሂጃ 11 እስከ 13 አያመ ተሽሪቅ ቀናት ደግሞ በሶስቱም ምሰሶዎች ላይ በቅደም ተከተል ሰባት ሰባት ጠጠሮች ይጣላሉ።
መንፈሳዊ መልዕክቱም የአረህማን እንግዶች ጠጠሩን በሚወረውሩበት ጊዜ “አላሁ አክበር” (አላህ ታላቅ ነው) በማለት ለአላህ ያላቸውን ፍጹም ታዛዥነት እና እጅ መስጠት ያድሳሉ።
እንደ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መረጃ ይህ ስነ ሰርዓት በአማኙ ልብ ውስጥ ያለውን የእምነት ጥንካሬ እና ከአላህ ውጪ ያሉ ተጽእኖዎች ደካማነት መሆናቸውን ያሳያል።
በአጠቃላይ የጀመራት ጠጠር ውርወራ ከመደበኛ ተግባርነቱ ባለፈ አማኞች በህይወታቸው ውስጥ የሚገጥሟቸውን የሰይጣን ፈተናዎች ለመቋቋም የሚያደርጉትን መንፈሳዊ ትግል እና ለአላህ መንገድ ያላቸውን ጽናት የሚያረጋግጡበት ታላቅ የጋራ መግለጫ ነው።