መንግሥት የማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ከመሰረቱ ለመፍታት በትኩረት እየሰራ ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግሥት በሀገራችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ከመሰረቱ ለመፍታት ግልጽ አቅጣጫ በማስቀመጥ ሲሰራ ቆይቷል አሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በነገሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያ ምርቃት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ መንግሥት ባለፉት ዓመታት የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን መሰረታዊ የሆኑ ችግሮች ለመፍታት በቁርጠኝነት ሲሰራ ቆይቷል፡፡
በዚህም ግልጽ እቅድና አቅጣጫ በማስቀመጥ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ከመሰረታቸው ለመፍታት ሰርቷል ነው ያሉት፡፡
ችግሮች በሂደት እየተፈቱ መሆናቸውን አንስተው÷ ይህም ትልቅ ተስፋ መሰነቅ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለይም በግብርናው ዘርፍ የመጡ ለውጦች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን በመጥቀስ በኢንዱስትሪ፣ ማዕድን እና ቱሪዝም መስኮች ከፍተኛ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በምስራቅ ቦረና ዞንም በትምህርት፣ ጤና፣ መሰረተ ልማት እና የውሃ አቅርቦትን ከማሳደግ ረገድ ሰፋፊ ስራዎች መሰራታቸውን አመልክተዋል፡፡
የለውጡ መንግሥት አካታችነትን መርሁ በማድረግ ከዚህ ቀደም ያልለሙ አካባቢዎችን በማልማት ላይ ይገኛል ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ÷ ለዚህም የገዳ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ይህ ጅምር ነው፤ መንግሥት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በትኩረት መስራቱን ይቀጥላል ነው ያሉት በመልዕክታቸው፡፡
በአቤል ነዋይ